አርዕስተ ዜና

በጫጫ ከተማ በቅርቡ የደረሰው የጎርፍ አደጋ ለቅድመ መከላከል ሰራ ትኩረት ባለመሰጠቱ ነው - አስተያየት ሰጪዎች

17 Jul 2017
1832 times

ደብረ ብርሃን ሀምሌ 10/2009 በሰሜን ሸዋ ዞን በአጎለላና ጠራ ወረዳ ጫጫ ከተማ በቅርቡ የደረሰው የጎርፍ ክስተት በከተማ አስተዳደሩ በኩል የቅድመ መከላከል ስራ ባለመሰራቱ የተፈጠረ መሆኑን አደጋው የደረሰባቸው ነዋሪዎችና የስራ ኃላፊዎች ገለፁ ።

 በከተማው ሰሞኑን በደረሰ የጎርፍ አደጋ  በግለሰቦችና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ግምቱ በውል ያልታወቀ ንብረት ሲወድም በመስሪያ ቤቶች መዛግብት ለብልሽት ተዳርጓል ።

 በጫጫ ከተማ በሆቴል ንግድ ስራ የተሰማሩት ወይዘሪት ቤተልሄም መሐመድ እንደገለፁት ሰሞኑን በከተማው ለደረሰው የጎርፍ ክስተት ምክንያቱ በከተማ አስተዳደሩ በኩል የቅድመ አደጋ መከላከል ስራዎች አለመሰራታቸው ነው ።

 "የክረምቱን መግባት ተከትሎ የተደፈኑ የመንገድ ዳር ተፋሰስ መውረጃዎች ከፈታ፣ ጠረጋና ጥገና የመሳሰሉ የአደጋ ጠጋላጭነት ቅድመ መከላከል ስራዎች አለመሰራታቸው  ለችግሩ መንስኤ ነው " ብለዋል ።

 የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ በሚከራዩ ክፍሎች ውስጥ የነበሩ አልጋዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

 አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሆቴላቸውን ስራ በማቆም የጥገናና ቁሳቁስ የማሟላት ስራ እንዲያካሂዱ መገደዳቸውን አስረድተዋል።

 ወይዘሮ ዘውዴ ሞገስ የሚባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ከመኖሪያ ቤታቸው ዘልቆ በገባው ጎርፍ የምግበ እህልን ጨምሮ ቁሳቁስ የወሰደባቸው መሆኑን ገልፀዋ ።

 የከተማው የመንገድ ዳር ተፋሰስ አለመሰራት ለአደጋው ክስተት ምክንያት መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ ዘውዴ የከተማው አስተዳደር ለችግሩ ተጠያቂ ቢያደርገውም ለአደጋው ተጠቂዎች የእለት ደራሽ እርዳታ ለማቅረብ ጥረት አለማድረጉ ሌላው ቅሬታ የፈጠረ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 የአጎለላና ጠራ ወረዳ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ከፈለኝ ድባቤ በሰጡት አስተያየት የከተማው ተፋሰስ ባለመስራቱ  በተከሰተ ጎርፍ በፍርድ ቤቱ በቀጠሮ ላይ የነበሩትን ጨምሮ 780 የወንጀልና የፍትሃብሄር ፋይሎች ለብልሽት ተዳርገዋል ።

 "በተጨማሪም በአምስት ኮምፒውተሮች ውስጥ የነበሩ መረጃዎች ለተመሳሳይ ብልሽት ተዳርገዋል" ብለዋል።

 አዲስ ክሶችንም በዘመናዊ መረጃ ስርአት መመዝገብ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ላለፉት ስድስት ቀናት አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱን ጠቁመዋል ።

 የከተማው ማዘጋጃ  ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሲራክ ጌታነህ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በከተማው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ ከአራት ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውሰጥ መንገድ ግንባታ ተካሂዷል ።

 ይሁንና ከመንገዱ ጋር ተያይዞ መገንባትና መጠገን የነበረባቸው የተፋሰስ መውረጃዎች በወቅቱ አለመሰራታቸውን ተናግረዋል።

 ባለፈው ሰኔ ወር 2009 ዓ .ም በግማሽ ሚሊዮን ብር የተፋሰስ መውረጃ ቦይ ግንባታ ለማካሄድ ስራው ለተደራጁ ማህበራት ቢሰጠም  በማህበራቱ በኩል "ጊዜው ዘግይቷል" በሚል ስራውን ማካሄድ አለመፈለጋቸውን ተናግረዋል ።

 "የተፋሰስ መውረጃ አለመሰራቱ ለችግሩ መንሰኤ ነው "ያሉት ስራ አስኪያጁ ችግሩን በጊዚያዊነት ለመፍታት ከባለሀብቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን የተፋሰስ ከፈታና ፅዳት ሰራ መጀመሩን አስታውቀዋል

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ