አርዕስተ ዜና

እግረኞች ስለ መንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንቡ ግንዛቤ ሊፈጠርላቸው ይገባል

17 Jul 2017
1030 times

 አዲስ አበባ  ሀምሌ 10/2009 የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ስለወጣው የትራፊክ ደንብም ሆነ ስለሚተገበርበት ሁኔታ እንደማያውቁ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።

 የሚመለከታቸው አካላት በበኩላቸው የእግረኛ መንገዶችና ማቋረጫዎች እስኪሟሉና የህብረተሰቡ ግንዛቤ እስኪጎለብት ደንቡ ተፈጻሚ አይሆንም ብለዋል።

 ኢዜአ ስለጉዳዩ ያነጋገራቸው አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ፣ ወጣት ናኦድ ነገሰ፣ ወይዘሮ ሳራ ደሳለኝና ሳጂን ታከለ አይዛ፤ በአሽከርካሪዎችና በእግረኞች ጥፋት የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ስለመውጣቱም ሆነ ስለ አስገዳጅነቱ እንደማያውቁ ነው የገለፁት።

 የትራፊክ ህግ አክብረው መንገድ የማይጠቀሙ እግረኞች ላይ ጭምር ቅጣት የጣለው የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 የፀደቀው ታህሳስ 2009 ዓ.ም ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል።

 ሌሎቹ አስተያየት ሰጪዎች ወጣት ናኦድ ነገሰ፣ ወጣት አሸናፊ ጴጥሮስ፣ አቶ ሙስጠፋ ሁሴንና ቄስ ታደሰ መንግስቱ ደግሞ ደንቡ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ለህብረተሰቡ የማሳወቅ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

 የህብረተሰቡን የማይቋረጥ እንቅስቃሴና ተለዋዋጭነት ከግንዛቤ ያስገባ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል።

 የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ እና የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ደንቡን ለማስተግበር ለእግረኞች ግንዛቤ የመፍጠርና ምቹ የመንገድና የማቋረጫ መሰረተ ልማት እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታመነ በሌ፤ ደንቡ ካለመታወቁም በላይ የእግረኞች መሻገሪያ የሌለባቸው ቦታዎች በመኖራቸው ደንቡን ለመተግበር እንደሚከብድ ነው የተናገሩት።

 የእግረኛ መንገድ ችግሩን ለመፍታትም የእግረኛ መሻገሪያዎች ግንባታ እንደታሰበበትና በአንዳንድ ቦታዎች ለሚገነቡትም ጨረታ መውጣቱን ጠቁመዋል።

 እንደ ፖሊስ ኮሚሽን ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የንቅናቄ ሥራ እየተሰራ መሆኑንና ህብረተሰቡ አንብቦ እንዲረዳም ደንቡን ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኘው ናቸው።

 በቅርቡ እንደሚፀድቅ የሚጠበቀው የደንቡ ማስተግበሪያ መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን በመመሪያው መሰረት የትራፊክ ደንቡን የተላለፈና ቅጣቱን ለመፈፀም ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም ገንዘብ ያልያዘ ተመጣጣኝ ማህበራዊ ሥራ እንዲሰራ ይገደዳል።

 የተባሉ የቅድመ ሁኔታ ስራዎች ተጠናቀው ደንቡ ተግባራዊ ሲሆን ለእግረኛ ባልተፈቀደ መንገድና ማሳለጫ የተጓዘና ያቋረጠ፣ ቀለበት መንገድ ዘሎ ያቋረጠ፣ በጆሮው ማዳመጫ አድርጎ መንገድ ያቋረጠና በእግረኛ መንገድ ላይ ንግድ የነገደ 40 እና 80 ብር ይቀጣል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ