አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በትግራይ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚጠበቀውን ያህል እየተከናወነ አይደለም

17 Jul 2017
755 times

መቐለ ሐምሌ 10/2009 በትግራይ ክልል  የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚጠበቀውን ያህል እየተከናወነ እንዳልሆነ የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ባለሙያው አቶ ዘውደ ሀዋዝ እንደገለፁት በክልሉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተጀመረ አንድ አመት አስቆጥሯል፡፡

ምዝገባው በይፋ ከተጀመረበት ከሀምሌ  2008 ወዲህ የተመዘገበው  ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ  39 ሺህ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት አመቱ በክልሉ በጤና ተቋማት የተወለዱ ህፃናት ቁጥር 108 ሺህ ቢሆንም ወሳኝ ኩነት ተመዝግበው የልደት የምስክር ወረቀት የወሰዱ ግን 21 ሺህ ብቻ ናቸው፡፡

የችግሩ መንስኤ ደግሞ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደ መደበኛ ስራቸው ወስደው አለመስራታቸውና ሌሎች እንዲሰሩ ግፊትና ክትትል አለማድረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በ600 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥም ምዝገባው የተጀመረ ሲሆን ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚጎድለው ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ምዝገባ ባልተጀመረባቸው 61 የገጠር ቀበሌዎች ምዝገባውን ለማስጀመርና ምዝገባ የተጀመረባቸውን ለማጠናከር ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የህክምናና ክብካቤ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ በሪሁን መስፍን ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በተለይም ልደትና ሞት ቅፅ እንዲሞላ ለሁሉም ጤና ተቋማት ቢነገርም አፈፃፀሙ ደካማ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ''በልደትና ሞት አመዘጋገብ ላይ ያለውን ክፍተት ለማስተካከል ቢሮው በቀጣይ ተጨማሪ ስራዎችን ይሰራል''  ብለዋል፡፡

የወረዳ አስተዳደሩ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንደሌላው የልማት ስራ በቅንጅት እንዲመራ በማድረጉ ስራውን በተሻለ መንገድ ለመፈፀም ተችሏል ያሉት ደግሞ የታህታይ አድያቦ ወረዳ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ባለሙያ አቶ ገብረ ሀዋሪያ ታደሰ ናቸው፡፡

በወረዳው በበጀት አመቱ ከተወለዱ 969 ህፃናት ኣብዛኛዎቹ ወሳኝ ኩነት ተመዝግበው የልደት የምስክር ወረቀት እንዲወስዱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ስራውን በተሻለ መንገድ ለመፈፀምና ስርአት ሆኖ እንዲቀጥል ደግሞ ለ18 ቀበሌ ገበሬ ማህበራት የክብር መዝገብ ማስቀመጫ ሸልፍ በማሰራት እንዲሰራጭ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ስራው በቅንጅት ሊመራ ባለመቻሉ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የላእላይ አድያቦ ወረዳ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ባለሙያ አቶ ሀጎስ ገብረ ስላሴ ናቸው፡፡

በዚህም ምክንያት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዝቅተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ በሶስት የቀበሌ ገበሬ ማህበራት እስካሁን ምዝገባ እንዳልተጀመረ አስረድተዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ