አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

65 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል…የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን

19 Jun 2017
516 times

ሰኔ 12/2009 እኤአ በ2017 መጀመሪያ 65.6 ሚሊዮን ሰዎች በጦርነትና መሰል ችግሮች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ይፋ አደረገ፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያስረዳው ከተፈናቃዮች መካከል 22.5 ሚሊዮኑ ስደተኞች ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት  እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነው፡፡

በጦርነትና መሰል ጉዳዮች በመላ ዓለም በየደቂቃው 20 ሰዎች ከቀያቸው እንደሚፈናቀሉም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ከዓለማችን ስደተኞች ውስጥ 55 በመቶ ያህሉ የደቡብ ሴዳን (1.4 ሚሊዮን)፣ የአፍጋኒስታንና (2.5 ሚሊዮን)  የሶርያ (5.5 ሚሊዮን) ዜጎች መሆናቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሶርያና ኢራቅ ቀውስ፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፣ ናይጄሪያና ደቡብ ሱዳን  የተከሰቱት  ግጭቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ማፈናቀላቸውንም ነው ሪፖርቱ ያብራራው፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  የስደት ቀውሱ እያሻቀበ ከሚገኝባቸው ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምነት የተሰለፈችዋ ደቡብ ሱዳን  በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎቿ ወደ ጎረቤት ኡጋንዳ ተሰደውባታል፡፡

ከስደተኞች ቁጥር አንጻር በዚህ ዓመት ሀገሪቱ ለስደተኞች መሰረታዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋት ገንዘብ ውስጥ 17 በመቶ ያህሉን ብቻ ማግኘቷም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በርካታ ስደተኞችን ላስጠለሉ ሀገራት ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ለመምከር የዓለም መሪዎች ባለፈው ሳምንት ካምፓላ ውስጥ ተመካክረዋል፡፡

በውይይቱም የኖርዌይ ስደተኞች ምክር ቤትዋና ጸሃፊ ጃን ኤገላንድ“የአሜሪካ፣አውስትራሊያና የአውሮፓ መሪዎች አጥር ቢያቆሙና ልዩ ልዩ መሰናክሎችን ቢያስቀምጡም” የስደት ቀውስ አለመገታቱን ገልጸው  ሀገራቱ ቀውሱን ከእይታቸው ውጪ ቢያደርጉትም  ችግሩ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ህሊና እንዳልጠፋ ተናግረዋል ፡፡

ዋና ጸሃፊው እንዳብራሩት የበለጸጉና የተረጋጉ የአውሮፓና አሜሪካ ሀገራት ስደተኞች እንዳይደርሱባቸው የቻሉትን ሁሉ ከማድረጋቸው ባሻገር በደሃ ሀገራት ለተጠለሉትም የሚፈለገውን ያህል ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ ብለዋል፡፡

እያሻቀበ የመጣው የተፈናቃዮች ቁጥር ፖለቲካዊ እልባት እንዲያገኝ  በቁርጠኝነት መስራት፣ ሰብዓዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚደረገውን ድጋፍ ማሳደግና ሁሉም ሀገራት የተጠያቂነት ድርሻቸውን እንዲወስዱ ማነቃቃት እንደሚያስፈልግም ነው የኖርዌይ ስደተኞች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ  ያብሩት፡፡

ዓለም የገጠማትን ፈተና ለመቋቋም ሁሉም ሀገራት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ26 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከ850 ሺህ በላይ የተለያዩ  ሀገራት ዜጎችን አስጠልላለች።

ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ቀን "አጋርነት ለስደተኛ ወገኖቻችን" በሚል መሪ ሀሳብ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጉኘየል የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በነገው ዕለት ይከበራል፡፡

 

ምንጭ፡- UNHCR፣CGTN Africa፣ኢዜአ

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ