አርዕስተ ዜና

ለካንሰር ሕክምና ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ ‘ሕይወታችን አደጋ ላይ ነው’... የካንሰር ሕሙማን Featured

18 Jun 2017
512 times

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2009 ለካንሰር ሕክምና ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ ‘ሕይወታችን አደጋ ላይ ነው’ ሲሉ የካንሰር ሕሙማን ገለጹ።

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በበኩሉ ከታማሚው ቁጥር አንጻር ማዕከሉ የሕክምና መሣሪያና ቦታ እጥረት በማጋጠሙና ሕሙማኑ በወቅቱ ተገቢውን ሕክምና ባለማግኘታቸው ከተመዘገቡት መካከል ከ23 እስከ 25 በመቶ የሚሆኑት ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ ብሏል። 

የማሕፀን በር ካንሰር ታማሚ የሆኑ አክስታቸው ወይዘሮ ፀሐይ አሊን በማስታመም ላይ የነበሩት አቶ አሊ ይማም ለካንሰር ሕክምና አገልግሎት የተመዘገቡት ከሁለት ዓመት በፊት ቢሆንም አገልግሎት ያገኙት ግን ከ6 ሳምንት በፊት እንሆነ ተናግረዋል። 

የአፍንጫ ስር ካንሰር ታካሚዋ ወይዘሪት እታገኝ ጌትነት በበኩሏ ሕክምናውን ለማግኘት የተመዘገበችው በ2007 ዓ.ም ቢሆንም ወረፋው የደረሳት ግን ከሦስት ሳምንታት በፊት እንደሆነ ገልጻለች።

አቶ አሊ ይማምና ወይዘሪት እታገኝ ጌትነት ታማሚዎች ሕክምናውን በወቅቱ ባለማግኘታቸው በርካቶች ለሕልፈተ ሕይወት እየተዳረጉ መሆናቸውን በሆስፒታሉ ቆይታቸው የታዘቡትን ገልጸዋል።

በዚህም መንግሥት ለካንሰር ሕክምና ትኩረት በመስጠት ሕሙማንን ሊታደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የካንሰር ሕክምና ማዕከል የካንሰር ህክምና ባለሙያና የጨረራ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ወንድማገኝ ጥግነህ እንደገለጹት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በቅድመ ካንሰር መከላከል ላይ አልተሰራም።

በዚህም ሕክምና ለማግኘት ከሚመጡት ታካሚዎች መካከል 70 በመቶዎቹ የካንሰር ሥርጭቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የጨረራ፣ የቀዶ ጥገና፣ የኬሞቴራፒ እና የመሳሰሉ የሕክምና አገልግሎቶች ያስፈልጋቸዋል።

ማዕከሉ ባለው የጨረራ መሣሪያዎች እጥረት ታካሚዎቹን በወቅቱ ማስተናገድ ባለመቻሉ ከተመዘገቡት ሕሙማን መካከል ከ23 እስከ 25 በመቶዎቹ ለሕልፈት እንደሚዳረጉ ነው ዶክተር ወንድማገኝ የገለጹት።

በማዕከሉ ካሉት ሁለት የጨረራ መሣሪያዎች አንዱ ከተበላሸ ሁለት ዓመታት እንዳስቆጠረ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አንደኛውም ለ3 ሳምንታት ተበላሽቶ የነበረ በመሆኑ ከሕሙማን ቁጥር አንጻር በቂ አይደለም ያሉት ዶክተር ወንድማገኝ፣ ይህም ለካንሰር ሕክምና ትኩረት አለመሰጠቱን ያሳያል ብለዋል። 

በማዕከሉ የጨረር ሕክምና ባለሙያ አቶ ሰለሞን ተሾመ በበኩላቸው “ማዕከሉ ብቸኛው የጨረራ አገልግሎት ሰጭ በመሆኑ በርካታ ዜጎች ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት አገልግሎቱን ባለማግኘታቸው ሲንገላቱ ይስተዋላል” ብለዋል።

በማዕከሉ የጨረራ ማመንጫ መሣሪያ ብልሽት ሲገጥመው የጥገና ባለሙያ ባለመኖሩ አገልግሎት እንደሚቋረጥና ዘላቂ መፍትሔ እየተሰጠ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአምስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ሕክምና ማዕከል እንደሚቋቋም ከተነገረ ዓመታት ቢቆጠሩም እስካሁን የሕክምና ክፍል ግንባታ ካጠናቀቀው ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ውጭ ሌሎቹ አልጀመሩም።

እ.አ.አ በ2016 የወጣው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በዓመት 60 ሺህ ሰዎች በካንሰር በሽታ የሚያዙ ሲሆን ከነዚህ መካከል 44 ሺህ ተጠቂዎች ወይም 73 በመቶዎቹ ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ ለህልፈት ይዳረጋሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ