የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የዲግሪ ትምህርት ፕሮግራም ሊጀምር ነው

18 Jun 2017
620 times

አዳማ ሰኔ 11/2009 የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በፖሊሳዊ ሣይንስ የዲግሪ ኘሮግራም እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

በኮሌጁ የአቅም ግንባታ ስልጠና የተከታተሉ አንድ ሺህ 67 የፖሊስ አባላት ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኮሌጁ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለገሰ በተለይ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኮሌጁ እስካሁን በፖሊሳዊ ሣይንስ በዲኘሎማ የሚሰጠውን ትምህርት ከመጪው ዓመት ጀምሮ ወደ ዲግሪ ከፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል።

የዲግሪ መርሃ ግብሩ መከፈት የወንጀል ድርጊትን ለመከላከል  በጥበብ፣ በእውቀትና በክህሎት የበቁ አባላትን በየደራጃው ለማፍራትና ፖሊሳዊ አገልግሎቶችን ለማዘመን  ያስችላል፡፡

''ፖሊስ ማንኛውንም ህብረተሰብና ተቋም የሚያገለግል እንደመሆኑ የትምህርት ኘሮግራሙ መከፈቱ እነዚህን አካላት ለማርካት የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው ያስችላል'' ብለዋል፡፡

በተለይ ከተለመደና ኋላቀር አሰራር ፈጥኖ በመውጣት አሁን ካለው ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ ለመጓዝ አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኮሌጁ በስራ ላይ ያሉትንና በፖሊሰ ሣይንስ ዲፕሎማ ያላቸውን አባላት በመመልመልና የመግቢያ ፈተና በመስጠት ከ2010 ጀምሮ በዲግሪ ደረጃ ማሰልጠን ይጀምራል።

ኮሌጁ ከመደበኛው ጎን ለጎን የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመው የእለቱ ተመራቂዎችም ለአምስተኛ ጊዜ ለሁለት ወራት የተሰጠውን ስልጠና ተከታትለው ያጠናቀቁ ናቸው፡፡

ስልጠናውን ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ትራፊክ ፖሊሶች፣ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ኃላፊዎች እንዲሁም መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ተከታትለዋል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል አዱኛ ደበሌ በምረቃው ላይ እንደተናገሩት ፖሊስ ህገ መንግስቱን በማክበርና በማስከበር የሕዝቡን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር ለሀገሪቱ ህዳሴ እውን መሆን እየሰራ ነው።

በየደረጃው ያሉትን አባላት በስልጠናና በቁሳቁስ በማጠናከር በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት መስፈን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ