አርዕስተ ዜና

ወቅታዊና ችግር ፈቺ ጥናቶች እንዲካሔዱ የሚደረገው ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል ተባለ

16 Jun 2017
326 times

 አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 ወቅታዊና ችግር ፈቺ ጥናቶች በስፋት እንዲካሔዱ የሚደረገውን ድጋፍ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

ይህ የተገለፀው ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የግልና የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ያሳተፈበት 16ኛው ዓመታዊ ዘርፈ ብዙ ጥናታዊ ኮንፍረንስ ሲካሄድ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አረጋ ይርዳው እንደገለፁት በአገሪቱ የተመራማሪዎችን ትኩረትና ቁርጠኝነት የሚሹ በርካታ ችግሮች በመኖራቸው ጥናቶች እንዲካሔዱና መፍትሔም እንዲበጅላቸው መደገፍና አጥኚዎችንም ማበረታት ያስፈልጋል።

የምርምና የጥናት ውጤቶች እንዲተገበሩና ለአገሪቱ ልማት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግም የተጠናከረ ክትትል ማድረግ ይገባል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በዕውቀትና በክህሎት የዳበሩ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ዕድገት ለመስራት ቁርጠኛና ሀላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች በማፍራቱ ረገድ የሚኖራቸውን ሚናም ጠቅሰዋል ዶክተር አረጋ።

ለዚህም ጥራታቸውን የጠበቁና ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችን በመደበኛነት ማከናወን እንደሚገባቸው ነው የጠቆሙት።

እንደ ዶክተር አረጋ ገለጻ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኮንፈረንሱ የሚያደርጉት ውይይት ለልማት ጠቃሚ የሆኑ አብይና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችሏቸው ናቸው።

ከውይይቱ የሚገኙ የልምድ ልውውጦችና የዕውቀት ሽግግርም ለተቋማቱ አስፈላጊ መሆናቸውን አክለዋል።

እስከ ነገ በሚቀጥለው ኮንፍረንስ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በፋይናንስ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ጥናቶች እንሚቀርቡ ተገልጿል።

ከሚቀርቡት ጥናቶች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተካሔዱ ሲሆኑ ታትመው ለባለድርሻ አካላት እንደሚሰራጩም ተነግሯል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ