አርዕስተ ዜና

ስዊድን የእናቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና እንዲሻሻል የሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሰጠች Featured

20 May 2017
440 times

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 ስዊድን ለኢትዮጵያ እናቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎትና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ማሻሻያ የሚውል የ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች።

በተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ራኮቶ ቪክቶርና በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ የልማት ትብብር ኃላፊ ሚስስ አኒካ ጃያዋርድና የድጋፍ ስምምነት ተፈርሟል።

ሚስተር ራኮቶ ስዊድን የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ፕሮግራም ከግብ ለማድረስ ያደረገችውን የገንዘብ ድጋፍ አድንቀዋል።

የገንዘብ ድጋፉ አገሪቷ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሶማሌና ሐረሪን ሳይጨምር በስምንት ክልሎች የእናቶችን የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎትና ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማሻሻል እንደሚውል አረጋግጠዋል።

ይህም በአገሪቷ የሚወልዱ እናቶችን ሞትና ድህነት በመቀነስ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ የምዕተ ዓመቱን ዘላቂ ልማት ከግብ ለማድረስ ያስችላታል ነው ያሉት።

የኤምባሲው የልማት ትብብር ኃላፊ ሚስስ አኒካ በበኩላቸው እንዳሉት የገንዘብ ድጋፉ ለጤና ተቋማት መሳሪያዎች ግዥ፣ ለአምቡላንሶች አቅርቦት፣ ለፊስቱላ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ይውላል።

በሴቶች ላይ የሚፀመውን ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለማስቀረት፣ ያላቻ ጋብቻን ለማስቆም፣ እንዲሁም የሴቶች ግርዛትን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረትና የወሊድ ቁጥጥርን ለማሻሻልም እንዲሁ።

በተጨማሪም የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት በማሳደግና የፖለቲካ ተሳትፏቸውን በማሳደግ መብታቸውን ማረጋገጥ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

ድጋፉ በተወሰነ መልኩ ለወጣቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎትና የትምህርት ዕድል ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በጋምቤላና ሌሎች ስደተኞች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ለሰብዓዊ እርዳታ ይውላልም ብለዋል።

ስዊድን በኢትዮጵያ እያደረገች ያለው የልማት ፕሮግራም ድጋፍ ለስምንተኛ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል።

 

  

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ