አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የቅዱስ ያሬድ ስራዎች ለቱሪዝም ልማት እንዲውሉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመለከተ

19 May 2017
830 times

አክሱም ግንቦት 11/2009 የቅዱስ ያሬድ ስራዎች ለሀገሪቱ  የቱሪዝም ልማት  እንዲውል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ  ተመለከተ፡፡

በአክሱም ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው አውደ ጥናት "የቅዱስ ያሬድ ሰራዎች"  በማስመልከት የአዲስ አባባ፣የመቀሌና የአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች አቅርበዋል።

" ቅዱስ ያሬድ ለቱሪዝም ልማት ያበረከተው አስተዋጽኦ" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተማራማሪ ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ እንዳሉት፣የቅዱስ ያሬድ ስራዎች ለኢትዮጵያዊያን የፅናት፣የትዕግስትና የአዋቂነት ተምሳሌት ናቸው።

የቅዱስ ያሬድ መጽሐፍት፣የማህሌት ዜማ ፣የዜማ መሳሪያዎችና ትምህርት የሰጠባቸው ስፍራዎች ለቱሪዝም ልማት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ውድ ቅርሶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ቅርሶች ይበልጥ ለቱሪዝም መስህብነት እንዲውሉና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው በሰነድ መያዝ ይገባል፡፡ 

ከፍልስፍናዎቹ  የዓላማ ጽናትን፣ከውድቀት መነሳትን፣ ማደግና ምኞት ማሳካት መቻልን በተግባር መማር  እንደሚቻል ያመለከቱት ዶክተር ሙሉጌታ " ስራዎቹና ቅርሶችንም አጣምሮ የሚይዝ ዘመናዊ ሙዚየም  መገንባት ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው፣ ቅዱስ ያሬድና ስራዎቹን ለማስተዋወቅ የተጀመረው ጥረት ከግብ ለማድረስ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

" የቅዱስ ያሬድ ያስተማረባቸው ስፍራዎች፣የዜማ ስልቶችና የዜማ መሳሪያዎች መሰባሰብ  ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰፊ ስራ ይጠበቃል"  ያሉት አቶ አለማየሁ ስራዎቹ እንዲጠበቁና  ዘመናዊ ሙዚየም እንዲገነባ  መስሪያ ቤታቸው  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ይህንን አኩሪ ታሪክና ስራዎች  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ልማት እንዲውሉ መስራት እንዳለባቸው ያመለከቱት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅዱስ ያሬድ፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስነ ጽሑፍና ብራና ጥናቶች ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ሐጎስ አብርሃ ናቸው።

"የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅዱስ ያሬድ ጽሑፎችን በመሰብሰብና ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በመተርጎምና በሰነድ በመያዝ ጥቅም ላይ እንዲውል እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ስራዎችና የግእዝ ቋንቋን ለሀገሪቱ  የቱሪዝም ልማት  ጥቅም ላይ እንዲውሉ መነቃቃት ለመፍጠር በአክሱም ከተማ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ዛሬ የተጠናቀቀ ሲሆን ምሁራን፣ ተዋቂ  አርቲስቶች፣የሃይማኖት አባቶችና የመንግስት አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ