አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የፓስፖርት እደላ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት መሰጠት ጀመረ

19 May 2017
777 times

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 የፓስፖርት እደላን በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኩል ማድረጉን የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያውና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ስራውን በጋራ ለመከወን ተስማምተዋል።

ተቋማቱ የፓስፖርት እደላ ስራውን በደረሱበት ስምምነት መሰረት እያከናወኑ ስለመሆኑ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ መሰረት ፓስፖርት የማውጣት ሂደቱ በኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ የሚፈጸም ሲሆን እደላውን የኢትዮጵያ ፖስታ  አገልግሎት ድርጅት ያከናውነዋል።

የመምሪያው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘላለም መንግስቴ የስምምነቱ ዋና ዓላማ ደንበኞች ጥራት ያለውና ተደራሽ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም “የዋና መምሪያው ግቢ ካለበት የቦታ ጥበት የተነሳ እደላው ለፖስታ አገልግሎት ድርጅት መሰጠቱ በተገልጋዮች ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት ያስቀራል” ብለዋል።

የድርጅቱ የድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደለ አሰፋ በበኩላቸው የፓስፖርት እደላ ስርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ድርጅቱ አዲስ አደረጃጀት ማዋቀሩን ተናግረዋል።

የፓስፖርት እደላ አገልግሎቱ ከግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዋናው ፖስታ ቤት በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይም በመዲናዋ ለደንበኞች አመቺ በሆኑና በተመረጡ የድርጅቱ ጣቢያዎች ጭምር ይደረጋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በአገልግሎት መስጫ ማዕከሉ ለፓስፖርት እደላ ብቻ የሚያገለግል ቢሮና የእንግዳ ማረፊያ መገንባቱንና ለተገልጋዮችም ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተመልክቷል።

በማዕከሉ የፓስፖርት እደላ አገልግሎት ያገኙት ወይዘሮ ታምሬ ሙህዲንና አቶ ዳዊት ፈቃዱ አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ መሆኑንና ቀደም ሲል የነበረውን መንገላታት እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

አገልግሎቱን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ ጥናት መደረጉ በመግለጫው ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በአገር አቀፍ ደረጃ በ940 መደበኛና በአንድ ሺህ ወኪል ፖስታ ቤቶች አማካኝነት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ