አርዕስተ ዜና

እየተበራከቱ የመጡ የስርቆት ወንጀሎችን በጋራ ልንከላከል ይገባል

21 Apr 2017
294 times

ሚያዝያ 13/2009 በከተማችን እተበራከቱ የመጡ የወንጀል ድርጊቶችን ለመቆጣጠር በየአካባቢው የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ አገልግሎት የሚሰጡ ጣቢያዎች እያየን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው እና በየሰፈሩ የሚከሰቱ የተለያዩ የስርቆት አይነቶችም የዛኑ ያህል እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡

በህግ ቋንቋ ውንብድና የሚባሉት የሞባይል ነጥቆ መጥፋት፣ ጨለማን ተገን በማድረግ መዝረፍ፣ ማጅራት መምታትና የመሳሰሉ ወንጀሎችን መፈፀም በየሰፈሩ እየተለመዱ የመጡበት ሁኔታ ይታያል፡፡

በህግ አስከባሪ ብቻ ወንጀልን መከላከል አይቻልምና ህብረተሰቡ የበለጠ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል እያልን በህብረተሰቡና በፖሊስ ቅንጅት ውጤት ያስገኘ አንድ የውንብድና የቅጣት ውሳኔ ላካፍላችሁ፡፡

ውሳኔው የተሰጠው ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው፡፡

ታህሳስ 28 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት አቶ ዳግም ምስጋናው ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ዳግም ትንሳኤ ሆቴል አካባቢ  በሰላማዊ መንገድ በመጉዋዝ ላይ  ናቸው፡፡

ሶስት ጎረምሶች ጨለም ያለውን ስፍራ በመጠቀም በቦክስ ያጣድፏቸው ጀመር፡፡ አቶ ዳግም በተደጋጋሚ በፊታቸው ላይ ያረፈውን የቦክስ ውርጅብኝ ሊቋቋሙ አልቻሉም፡፡ 

ራሳቸውን ስተው ይዘረራሉ ፡፡ በዚህ ጊዜ ወጠምሻዎቹ ከኪሳቸው የነበረውን ግምቱ 8ሺህ 800 ብር የሆነውን ሞባይል በመውሰድ ከአካባቢው ይሰወራሉ፡፡

በአካባቢው ህብረተሰብና በፖሊስ ክትትል ሶስቱም ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ይውሉና ጉዳያቸው ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ይቀርባል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው አንደኛ ወንጀል ችሎት 1ኛ ታመነ አሰፋ 2ኛ ምንተስኖት በየነንና 3ኛ አባተ ቦጋለን የተለያዩ የወንጀል ማቅለያ ምክንያቶችን በማሰማት እያንዳንዳቸው በሁለት ዓመት ከሶስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

እነዚህ ጎልማሶች በአሁኑ ወቅት  የተዘረጋውን ሰርቶ የመለወጥ መርህ በመከተል ለወንጀል ያዋሉትን የተባበረ ክንድ ተደራጅተው ለልማት ቢያውሉት ምንያህል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አያዳግትም፡፡

ወደ ስርቆት ወንጀል የተሰማሩ ወጣቶችን በተናጠል ሳይሆን በጋራ ልንከላከላቸው እንደሚገባ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ