አርዕስተ ዜና

ማዕከሉ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር ነው

21 Apr 2017
282 times

ሀረር ሚያዚያ 13/2009 በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የአየር ንብረት ተስማሚ የግብርናና ብዝሀ ሕይወት ጥበቃ የልህቀት ማዕከል ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚመጡ የዘርፉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀምር አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከፊታችን ሰኔ ወር ጀምሮ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለሚሰጠው ትምህርት ያዘጋጀውን ስርዓተ ትምህርት ከትናንት ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጪ ምሁራን በማስገምገም ላይ ነው።

የልቀት ማዕከሉ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ቦቤ በዳዴ በዕለቱ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በማዕከሉ የሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚሄድ የግብርና ሳይንስን በምርምርና ስርጸት በማስፋፋት የሚፈለገው ምርትና ምርታማነት ለማምጣት የሚያስችል ነው።

በመጪው ሰኔ ወር በሚጀመረው የአየር ንብረት ተስማሚ የግብርናና ብዝሀ ሕይወት ጥበቃ የትምህርት ፕሮግራም ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ  አገራት ያመለከቱ ተማሪዎችን የመመልመልና ስርዓተ ትምህርቱን የማስገምገም ሥራ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር ቦቤ ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ፣ የትምህርት ፕሮግራሙ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የሚሰጥ ሲሆን ከአገር ውስጥ፣ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የሚመጡ ብቃት ያላቸው መምህራን ተማሪዎቹን እንዲያሰለጥኑ ይደረጋል።

በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ፕሮግራሙ መጀመር ተቋሙ የሚሰጠውን የግብርና ትምህርት አንድ ደረጃ ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ የተቋሙ መምህራንና ተማሪዎች በተለያዩ የውጭ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች በመሄድ ልምድ እንዲቀስሙ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናና ብዝሀ ሕይወት ጥበቃ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።

"ማዕክሉ ከኢትዮጵያና ከመላው አፍሪካ የመጡ ተማሪዎች የሚሰለጥኑበት በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ዓለማቀፋዊነት ይዘት እንዲላበስ ያደርገዋል" ብለዋል

በስርዓተ ትምህርቱ ግምገማ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አሰፋ ታዓ፣ የምርምር ማዕከሉ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በምርምር ስርጸትና ኤክስቴንሽን ሥራ ለበርካታ ዓመታት በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የአየር ንብረት ተስማሚ የግብርናና ብዝሀ ህይወት ጥበቃ የልህቀት ማዕከል መከፈት ድርቅን ተቋቁመው ምርት የሚሰጡ ሰብሎችን ማውጣት የሚችሉ የግብርና ባለሙያዎችን ለማፍራት ያስችላል።

ከእዚህ በተጨማሪ የምርምር ችሎታ ያላቸውና አዳዲስ ቴክኖሎጂ የሚያወጡ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች እንዲፈልቁ የሚያደርግ መሆኑን ነው የገለጹት።

"ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ እያካሄዱት ያለው የምርምርና ስርጸት ሥራ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ማዕከሉ ከፍተኛ እገዛ ከማድረጉ ባለፈ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና አርሶአደሩ ተቀራርበው የሰሯቸው የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ለማስፋፋት መንገድ ይከፍታል" ብለዋል።

ከትናንት ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚዘልቀው የስርዓተ ትምህርት ግምገማ የአገር ውስጥና የውጭ አገር መምህራንና ተመራማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አጋዥ የልማት ድርጅቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሳተፋቸው ታውቋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 2016 (እ.ኤ.አ)  የአፍሪካ የአየር ንብረት ተስማሚ የግብርናና ብዝሀ ሕይወት ጥበቃ የልቀት ማዕከል ሆኖ መመረጡ ይታወሳል፡፡   

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ