አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የታክሲና ሃይገር አሽከርካሪዎቹ ለትራፊክ አደጋ መቀነስ የድርሻቸውን ይወጣሉ Featured

21 Apr 2017
343 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2009 የታክሲና ሃይገር አውቶቡስ አሽከርካሪዎች እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ሕግና ደንብ ከማክበር ባሻገር በመልካም ስነ-ምግባር እንደሚሰሩ ቃል ገቡ።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ለአሽከርካሪዎቹ በተሻሻለው የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብና የአሽከርካሪዎች ስነ-ምግባር ላይ ስልጠና እየሰጡ ነው።

ስልጠናው ሲጀመር በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች በተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች በዜጎች ላይ የደረሱ አሰቃቂ ጉዳቶችን የሚያሳዩ ዶክመንተሪ ፊልሞች ለዕይታ ቀርበዋል።

አሽከርካሪዎቹም በተመለከቱት አስከፊ ጉዳት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ዕንባቸውን በማፍስስ ሲገልፁ ተስተውለዋል።

በአንድነትም "በእኔ ስህተት የሰው ሕይወት አይጠፋም" ሲሉ ቃል ገብተዋል፤ አብዛኞቹ አደጋዎች በአሽከርካሪዎች ስህተት የተፈጠሩ በመሆናቸው ይህን ለመግታት ቁርጠኝነታቸውንም ገልጸዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች ከስልጠናው ባገኙት ግንዛቤ ለአደጋው መቀነስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የታክሲ አሽከርካሪው አቶ ደረጀ ተሾመ ስለ አሽከርካሪዎች ስነ-ምግባር የተነሱት ሀሳቦች አስተማሪ በመሆናቸው ተረጋግተው በማሽከርከር ህይወትና ንብረትን ከጥፋት ለመታደግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ሌላው አሽከርካሪ አቶ አቤል ሽፈራውም "በአጭር የስልጠና ጊዜ ሁሌም ተጥንቅቀን በማሽከርከር ከአደጋ እንድንጠበቅ የሚያስችል ትምህርት አግኝተናል" ብለዋል።

በሌላ በኩል የስልጠናው ተሳታፊዎች ለስነ-ምግባር ጉድለቶቻቸው መነሻ ናቸው ያሏቸውን ምክንያቶች አንስተዋል።

የእግረኞች ተገቢ ያልሆነ የመንገድ አጠቃቀም፣ የትራንስፖርት ታሪፍ ተመጣጣኝ አለመሆንና የትራፊክ ደንብ አስከባሪዎች የስነ-ምግባር ጉድለት ለአሽከርካሪዎች ስነ-ምግባር መጓደል መንስኤዎች ናቸው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ የትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ ለማ የትራፊክ አደጋውን ለመቀነስ  በአገር አቀፍ ደረጃ ህዝባዊ ንቅናቄ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዲናዋም የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከዕለት ዕለት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ በህይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የችግሩ መንስኤዎች የተለያዩ ቢሆኑም የህግ ማዕቀፉ መላላትና የአሽከርካሪዎች የስነ-ምግባር መጓደል በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ለአደጋው መባባስ የአሽከርካሪዎች ጥፋት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በመታወቁና እነሱን ማብቃት የመፍትሄው አካል በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

አሽከርካሪዎቹ ያነሷቸውን ችግሮች ለማቃለል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው የእግረኛ መንገዶችን ለማስተካከል ከአጋር አካላት ጋር እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ታሪፍን በተመለከተ የተካሄደው ጥናት መጠናቀቁንና በቅርቡም ውይይት ተደርጎበት እንደሚፀድቅ አቶ ዮሃንስ ጠቁመዋል።

የፌደራል ትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ንጉሱ ፍስሀ በበኩላቸው የስነ ምግባር ጉድለት የሚታይባቸው የትራፊክ ደንብ አስከባሪዎችን ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ለሶስት ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ከ4 ሺህ 500 በላይ የታክሲና ሃይገር አውቶቡስ አሽከርካሪዎች እየተሳተፉ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ