አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

መቀሌን ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመለከተ

21 Apr 2017
377 times

መቀሌ ሚያዝያ 12/2009 መቀሌን ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ስራ የተቀናጀ ባለመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመለከተ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት  በከተማው  ጎዳናዎች፤ በንግድ ማዕከላትና በተከለሉ አረንጓዴ ስፍራዎች የሚከናወኑ የፅዳት ስራዎች ህዝቡን በባለቤትነት ያላሳተፉና  ቅንጅት የጎደላቸው ናቸው።

ከነዋሪዎች መካከል አቶ ስዒድ መሓመድ ዓሊ ከሸቀጣሸቀጥ፣ አልባሳትና ጫማ መደብሮች የሚወጡ ካርቶኖች፣ ላስቲኮችና ሌሎች ደረቅ ቆሻሻዎች በግዴለሽነት በመንገድ ዳር እንደሚጣሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት  የከተማው ውበትና ፅዳት እንዲበላሽ ምክንያት ሆኗል ።

ከተለያዩ የንግድ ተቋማት መፀዳጃ ቤቶች የሚወጣው  ፍሳሽ ቆሻሻ  ከዋናው የመንገድ የተፋሰስ መውረጃ መስመር ጋር በመገናኘታቸው ለአካባቢ ብክለትና ለሰዎች ጤና ጠንቅ እየሆነ መምጣቱንም ጠቁመዋል ።

በወንዞች ዳርቻ የሚለሙ አትክልትና ፍራፍሬዎች በቀጥታ ለገበያ መዋላቸውም ነዋሪውን ለተቅማጥና ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ እያደረጋቸው ነው፡፡

አቶ አለማት አማረ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በከተማው በመንገዶች ዳር የመኪና እጥበት እየተስፋፋ በመምጣቱ ለከተማው የንፅህና ጉድለት የራሱን አስተዋጽኦ  ከማድረግ ባለፈ በንግድ ስራ እንቅስቃሴላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

"አካባቢያችን አረንጓዴ ለማድረግ በቤታችን ደጅ የምንተክላቸው የዛፍ  ችግኞች  ባለቤት በሌላቸው እንስሳት እየተበሉና በሰዎች ተቆርጠው ስለሚወሰዱ ተቸግረናል "ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ትዕበ አርአያ ናቸው።

እንደ አስተያት ሰጭዎቹ ገለፃ  ድርጊቱን በአግባቡ የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል አለመኖር ችግሩን አባብሶታል ።

በከተማው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የጤና ተቆጣጣሪ አቶ ያሬድ ተኸሉ  በበኩላቸው ከነዋሪዎቹ የተነሱ ቅሬታዎች ተገቢ መሆናቸውን ጠቅሰው  ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በቅንጅት ባለመሰራቱ ክፍተት መፈጠሩን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት ህብረተሰቡን ያሳተፈና ቀጠይነት ያለው ሳምንታዊ  የፅዳት ዘመቻ እንደሚካሄድ ፣  ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻን ያለአግባብ በሚያሶግዱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የቅጣት እርምጃ  እንደሚወሰድ አመላክተዋል ።

በከተማው አስተዳደር የፅዳትና ውበት ስራ ሂደት ባለቤት አቶ ገብረእግዚአብሄር ካሳ የከተማውን ውበትና ፅዳት ለመጠበቅ ዘጠኝ ማህበራት በማደራጀት ቆሻሻ የማስወገድ ስራና የፅዳት ዘመቻ ቢካሄድም ከከተማው ስፋት አንፃር በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ዘንድሮ በከተማው በተጀመረው የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር  የሚካሄደው  የከተማ ፅዳትና ውበት ስራ   አንዱ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም በተባባሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በተመደበ 23 ሚሊዮን ብር ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት ለመቀየር የተጀመረው ፕሮጀክት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አስተዋጽኦ እንዳለም ተጠቁሟል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ