አርዕስተ ዜና

ወጣቱ የተፈጠረውን ብሔራዊ መግባባት ተጠቅሞ ሃገር የመረከብ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተመለከተ

21 Mar 2017
524 times

ሀዋሳ መጋቢት 11/2009 ወጣቱ የተፈጠረውን ብሔራዊ መግባባት ተጠቅሞ ሃገር የመረከብ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን አመለከተ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ስድስተኛ ዓመት ፌደሬሽኑ በተለያዩ ፕሮግራሞች ለማክበር ተዘጋጅቷል፡፡

የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ወጣት የሺዋስ አለሙ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጸው ወጣቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፈጠረውን ብሄራዊ መግባባት ተጠቅሞ ሃገር የመረከብ ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡

ሀላፊነቱን  ለመወጣትም ሃገር የመገንባት፣የመውደድና ምክንያታዊ ሆኖ በጥቅሞቹ ዙሪያ የመጠየቅና የመሞገት ልምዱን ማሳደግ ይኖርበታል፡፡

የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም ወጣቱ በተደራጀ መልኩ ድጋፉን የሚያሳይበትና በአንድነት የሚንቀሳቀስበት እንደሚሆንም  ወጣት የሺዋስ ተናግሯል፡፡

ፌዴሬሽኑ ከክልሉ የህዳሴ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ከ85ሺ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ክልል አቀፍ ፕሮግራም  ማዘጋጀቱንም ጠቁሟል፡፡

ከዚህ ውስጥ 60ሺህ ያህል   ወጣቶች መሆናቸውን የጠቀሰው ፕሬዝዳንቱ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ የሚገኘውን የጥያቄና መልስ ውድድር ማጠቃለያ መጋቢት 16/2009ዓ.ም እንደሚሆን  አመልክቷል፡፡

በማግስቱ ለሃገሬ ልማት እሮጣለሁ በሚል ሃሳብ እስከ 6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና  25ሺህ  ያህል የተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር እንዲሁም  መጋቢት 21/2009ዓ.ም ደግሞ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ሌሎችም አካላት የሚካፈሉበት  የፓናል ውይይት  ይካሄዳል፡፡

በዚሁ እለት በሃዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም በሚካሄደው የማጠቃለያ ፕሮግራም ስፖርታዊ ውድድሮችና  የስነ ጽሁፍ ዝግጅቶች ይኖራል፡፡

የክልሉ ታላቁ  ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው በበኩላቸው በግድቡ ግንባታ የክልሉ ወጣቶች በአደረጃጀትና በግል ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

“የግድቡ ዋንጫ በክልሉ በሚንቀሳቀስበት ወቅት  ወጣቱ በግምባር ቀደምነት እየመራ ነው"  ያሉት አቶ ፋሲካ ፕሮግራሙ ወጣቱ የሃገሪቱ ህዳሴ ባለቤት እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ስድስተኛ ዓመት  በክልል ደረጃ በወላይታ ሶዶ መጋቢት 24/2009ዓ.ም  በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ተጠቅሷል፡፡

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ