አርዕስተ ዜና

የሴቶችን ሰብአዊ መብት ለማስከበር በተደረገው ጥረት ለውጥ ቢኖርም አሁንም ችግሮች እንዳሉ ተመለከተ

20 Mar 2017
614 times

ባህርዳር መጋቢት 11/2009 የሴቶችን ሰብአዊ መብትና እኩልነት  ለማስከበር  በተደረገው ጥረት ለውጥ ቢኖርም አሁንም ችግሮች እንዳሉ ተመለከተ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን  ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የአለም የሴቶች ቀንን በባህር ዳር ከተማ  በፓናል ውይይት አክብሯል።

" የዘንድሮው በዓል የሚከበረው የሴቶችን ገቢ ማሳደግ ለሰብአዊ መብቶቻቸው መከበር መሰረት ነው"  በሚል መሪ ሃሳብ መሆኑን በኮሚሽኑ  የሴቶችና ህጻናት ኮሚሽነር ወይዘሮ ኡባህ መሃመድ በበዓሉ ላይ ገልጸዋል፡፡ 

ይህም የሀገሪቱ  ሴቶች ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ በንቃት የመሳተፍና የመጠቀም መብት ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሯ እንዳመለከቱት ባለፉት ዓመታት በሴቶች የትምህርት ተሳትፎ፣ የመሬትና የሌላም  ሃብት ባለቤትነት መብቶችን ማስከበር ላይ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡

ሆኖም አሁንም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ  የመብት ጥሰቶችና ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

የሴቶችን ሰብአዊ መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር  ኮሚሽኑ ስምንት ቅርንጫፎችን ከፍቶ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ ያተኮረ  ግንዛቤ የማስጨበጥ   ስራ እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ  በበኩላቸው ባለፉት ስርዓቶች በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና  ለማስወገድ ሴቶች ከወንድ  አጋሮቻቸው ጋር  በመሆን ታግለው ማታገላቸውን ተናግረዋል።

ባስመዘገቡት ድልም የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት  እየጎለበተ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኮሚሽነር አቶ አበረ ሙጨ እንዳሉት ደግሞ  የሴቶችን የመብት ጥሰት ለማስወገድ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ነጻ የህግ አገልግሎት እንዲያገኙ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

ከዓለም ጤና ድርጅት የመጡት ዶክተር ፍቅር መለሰ በበኩላቸው በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን የጾታና ሌሎች የመብት ጥሰት ለማስወገድ ራሳቸው ሴቶች ደፍረው መታገል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ማዕከል  ወጣት ዘመኑ አጥናፉ በሰጠው አስተያየት የሴቶችን መብት ለማስከበር ያለው ክፍተት የህግ ማዕቀፍ ችግር ሳይሆን የህብረተሰቡ  ግንዛቤ ማነስና  የፍትህ አካሉ ቁርጠኝነት መጓደል  መሆኑን ተናግሯል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበር በዓል ብቻ ሳይሆን በየመስሪያ ቤቱ፣ በትምህርት ቤቶችና በሌሎችም የስራ አካባቢዎች የዕለት ተዕለት አጀንዳ መሆን እንዳለበት ጠቁሟል።

በባህር ዳር ከተማ በተከበረው የሴቶች ቀን በዓሉ ላይ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተወካዮች ፣የሃይማኖት አባቶችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ