አርዕስተ ዜና

ተጎጂ ቤተሰቦችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ርብርብ የሚያኮራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ Featured

19 Mar 2017
628 times

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2009 "ተጎጂ ቤተሰቦችን መልሶ ለማቋቋም ሕብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚያኮራ ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ከሌሎች ሚኒስትሮችና የአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ዛሬ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በተለምዶ ቆሼ በተባለው አካባቢ ተገኝተው መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት ላይ በደረሰው አደጋ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችን አጽናንተዋል።

አቶ ደመቀ፤ ሕብረተሰቡ አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ በስፍራው ተገኝቶ ተጎጂዎቹን መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለው ርብርብ የሚያኮራና የሚያበረታታ መሆኑን ነው የገለጹት።

''አደጋው የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ የሰበረና አሳዛኝ ነው'' ያሉት አቶ ደመቀ፤ በተለይ ደግሞ ሴቶችና ህጻናት ከተጎጂዎቹ መካከል ከፍተኛ ቁጥር መያዛቸው የበለጠ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስትም ይህንኑ በመገንዘብ ብሔራዊ የኃዘን ቀናት ከማወጅ ባለፈ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በከተማ አስተዳደሩ አማካኝነት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።

ህይወታቸው ያለፉ ዜጎችንም በተቻለው ሁሉ ስርዓተ ቀብራቸው እንዲፈጸም ማድረጉን ገልጸው፤ በቀጣይ የሚጠረጠር ቦታ ካለ "ፍለጋው ይቀጥላል ነው" ያሉት።

"መንግስትና ሕብረተሰቡ ተባብረው ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ይረባረባሉ" ብለዋል።

በተለይ ደግሞ አስከሬን በመለየትና በመፈለግ በጣም ፈታኝ የሆነ ስራ በመስራት የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጡ የቆዩ የአካባቢው ወጣቶች፣ ነዋሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ምስጋና እንደሚገባቸው በአጽንኦት ገልጸዋል።

በአካባቢው ያሉ ቤቶች በጥናት ላይ በተመሰረተ መንገድ እንደሚነሱ ገልጸው፤ "ዜጎች የተረጋጋ ህይወት እንዲመሰርቱ የማስቻል ስራም ይከናወናል" ነው ያሉት።

በአደጋው ምክንያት ችግር ያጋጠማቸው ሕጻናትም ትምህርታቸውን ጨምሮ ሌሎች መደበኛ ሕይወታቸውን የሚመሩበት መንገድ እንደሚመቻች ተናግረዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በተወሰነ መልኩ የጀመረው ስራ መኖሩን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አስጠንቶ ዘላቂ መፍትሄ የማዘጋጀት ስራም በትኩረት እያከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።

ኃዘኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ተጎጂዎቹን በዘላቂነት ማቋቋም እስከሚቻል ድረስ ሁሉም ሰው የድርሻውን ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ