አርዕስተ ዜና

ለተጎጂ ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍ እንደቀጠለ ነው

18 Mar 2017
464 times

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2009 የተለያዩ ክልሎችና ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በቆሼ በደረሰው አደጋ ለተጎዱ ቤተሰቦች መቋቋሚያ የሚሆን ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ዛሬ የገንዘብ ድጋፉን ተረክበዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር አንድ ሚሊዮን ብርና የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ፤ ተጎጂዎችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የአዳማ ከተማ አስተዳደር የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረግ ሲሆን፤ የሀረሪ ክልል በበኩሉ 504 ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል።

በተመሳሳይ የብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሲያደርግ፤ የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሰራተኞች በበኩላቸው   የ40 ሺ 381 ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደገለጹት፤ ጉዳቱ ከደረሰ ቀን ጀምሮ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ ከክልሎችና ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ከጉዳቱ የተረፉ ቤተሰቦች የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ ለማድረግ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወደፊትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደርና የቦሌ ኤርፖርት የፌዴደራል ፖሊስ አመራር አባላትና ሰራተኞች በአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦችና ጉዳቱ የደረሰበትን አካባቢ ጎብኝተዋል።

የተለያዩ የህፃናት አልሚ ምግቦች፣ የጤፍና የስንዴ ዱቄት፣ ፓስታ፣ ሞኮረኒና ዘይት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በማስተባበር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ ሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ለሴቶችና ህፃናት ንፅህና መጠበቂያ የሚያገለግሉ ዳይፐርና ሙዲስ እንዲሁም የተለያዩ አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

የሴቶችና ህፃናት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ፤ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳድርና የተለያዩ የህዝብ አደረጃጃቶች በጋራ 20 ሺህ ብርና ከ200 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የቤት ቁሳቁስና አልባሳት አስረክበዋል።

በተመሳሳይ የቦሌ ኤርፖርት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከ58 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

ተቋሞቹ ድጋፋቸውን በቀጣይነት አጠናክረው በመቀጠል ከጎናቸው እንደማይለዩ ለሃዘንተኞቹ ገልጸዋል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ