አርዕስተ ዜና

የተልተሌ ሆስፒታል ግንባታ በመጓተቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ

401 times

ነገሌ  መጋቢት 5/2010 በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ የተጀመረው የሆስፒታል ግንባታ በመጓተቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው በአካባቢው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የወረዳው አስተዳደር በበኩሉ የሆስፒታሉ ግንባታ በማጠናቀቅ ለህዝቡ አገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በተልተሌ ወረዳ የሚለሚ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ አስጌ አዶላ የሆስፒታሉ ግንባታ የተጀመረው ከሰባት ዓመት በፊት ቢሆንም እስካሁን ሳይጠናቀቅ በመቅረቱ ተገቢ እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቅሬታቸውን በየመድረኩ ቢያቀርቡም አሳማኝ ምላሽ ባለመሰጠቱ የሆስፒታሉ ግንባታ ስራ መጓተት አሁንም የህዝብ ጥያቄ  ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በጽኑ የታመሙና  ወላድ እናቶች  ለከፍተኛ ህክምና አገልግሎት ከ100 እስከ 300 ኪሎ ርቀት በመጓዝ ያቤሎ ፣ ሀገረማሪያምና ወላይታ ሶዶ በመጓዝ ለእንግልትና ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳረጉም አቶ አስጌ ተናግረዋል፡፡ 

ባሻ ወርቁ ሁንዴ የተባሉት የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው ለሆስፒታሉ የቀረበው  የግንባታ ማከናወኛ ቁሳቁስ ሜዳ ላይ ጸሀይና ዝናብ እየተፈራረቀበት ለብልሽት ተጋልጦ  እንደሚገኝ መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች ተመርጠው ስለግንባታው መዘግየት ቢጠየቅም በቅርብ ጊዜ ይጠናቀቃል ከሚል በስተቀር በተግባር የታየ ነገር እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡

" የአካባቢው ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት እያገኘን ያለንው ለመጓጓዝ እስከ 7 ሺህ ብር በመክፈል ሀዋሳ ፣ወላይታና ሀገረማሪያም ድረስ በመሄድ ለተጨማሪ ወጪ ለጉዳት በመዳረግ ላይ ነው "ብለዋል፡፡

የተልተሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብዱረህማን ቃሲም ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የሆስፒታሉ ግንባታ መጓተት የክትትል እና  የተቋራጮች ድክመት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ ችግሩ እንዲፈታ ለዞንና ለክልል መንግስት ጥያቄ በማቅረቡ ግንባታው እስካሁን ከሁለት ተቋራጮች ተቀምቶ ለሶስተኛ  የግንባታ ተቋራጭ መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው ዓመት አዲስ የተረከበው ተቋራጭ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ በመሆኑ  ግንባታው ተጠናቆ በቅርቡ ለህዝቡ አገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግንባታው በ2002 ዓ.ም. የተጀመው የተልተሌ ሆስፒታል በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ በሶስት  ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ  እንደነበር ተመልክቷል፡፡

 

Last modified on Wednesday, 14 March 2018 16:17
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን