አርዕስተ ዜና

የሰው ሰራሽ አካል ማምረቻና ማገገሚያ ተቋማት ተደራሽ ባለመሆኑ ጉዳተኞች እየተቸገሩ ነው--- የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም

438 times

 

አዳማ መጋቢት 4/2010 በሀገሪቱ የሰው ሰራሽ አካል ማምረቻና ማገገሚያ ተቋማት ተደራሽ ባለመሆኑ አካል ጉዳተኞች እየተቸገሩ መሆኑን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።

በተቋሙ የቁጥጥርና ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሪት አምሳል እሸቱ እንደገለጹት የሰው ሰራሽ አካል ማምረቻና ማገገሚያ ተቋማት ተደራሽነቱ ያለበት ደረጃ  ከመስከረም 2010ዓ.ም ባሉት ሶሰት ወራት  ውስጥ ፍተሻና ቁጥጥር ተደርጓል ፡፡

ቁጥጥሩ በዋናነት የተካሄደው በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ነው።

በአካል ጉዳተኞች ማህበራት ብሄራዊ ፌዴሬሽን የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማምረቻ ድርጅት እና የሚኪሊ ላንድ  የማህበረሰብ ልማት ማስልጠኛና ሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማምረቻ ተቋም ላይ ቁጥጥር ተደርጓል።

በተደረገው ቁጥጥር በአዲስ አበባ የሚገኙ የአካል ጉዳተኞች አብዛኞቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ይህንን እያወቀ የሰው ሰራሽ አካል በነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በከተማዋ እንዲስፋፉ ያደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን ባለሙያዋ  ጠቁመዋል።

በዚህም ምክንያት የመዲናዋ ህፃናት የሰው ሰራሽ አካልና አካል ድጋፍ በማጣት ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውና ለተደራራቢ የጤና ችግር መጋለጣቸውን አስታውቀዋል።

ቢሮው የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ከማካተት አንፃር በሴክተር መስሪያ ቤቶች ያደረገው ክትትል አነስተኛ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያዋ "በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን የሚመለከት የተደራጀ መረጃም የለውም" ብለዋል።

መስሪያ ቤቱ የሰው ሰራሽ አካል እና የአካል ድጋፍ ማደራጃ የቦርድ ሰብሳቢና የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም እንደመሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ አይደለም ተብሏል።

ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍና የማገገሚያ ማዕከላትን ለዜጎች ተደራሽ ከማድረግ አንፃር፣ ያሉቱም  በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ከመስራት አንፃር ትኩረት እንዳልሰጠም ነው የተመለከተው፡፡

የአካል ጉዳተኞች የጤና እንክብካቤ፣ የትምህርትና የሰራ እድል ተደራሽንትን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ ሙሉ ተሳታፊዎችና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስፈፃሚ አካላት ያላሰለሰ ጥረትና ቁርጠኝነት  እንደሚጠይቅ ተቋሙ በመፍትሄነት አስቀምጧል።

በህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የህፃናትና ሴቶች ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ሰኒያ ሳኒ በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞችን የመንቀሳቀስ ችሎታ ማሻሻልን መሰረት ያደረጉ ድጋፎች በየደረጃው ማስፋፋት እንደሚገባ  አሳስበዋል።

ተቋሙ የአካል ጉዳተኞች ብሄራዊ የድርጊት መርሃ ግብርን መሰረት በማድረግ የሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት በተቀመጠው የህግ አግባብ እየሰሩ መሆኑን በመፈተሻ በተለዩ ክፍተቶች ላይ የመፍትሄ ሃሳብ ለማስቀመጥ አልሞ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጰያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበር ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሪት ቃልኪዳን ሽመልስ " የመንቀሳቀስ ብቃትን ማሻሻል የአካል ጉዳተኞች በተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ለመሳተፍ ያላቸውን እድል ያሰፋል "ብለዋል።

 

Last modified on Wednesday, 14 March 2018 16:51
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን