አርዕስተ ዜና

መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሕዝብ አመኔታ ያገኙ የፍትህ አካላትን መገንባት ያስፈልጋል

401 times

አዲስ አበባ  መጋቢት 4/2010  መልካም አስተዳደር ለማስፈን በየደረጃው የህዝብ አመኔታን ያገኙ የፍትህ አካላትን መገንባት እንደሚገባ ተነገረ።

 

የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን 'የሙስና መከላከል ስትራቴጂና ቴክኒካል ሊደርሽፕ' በሚል ርዕስ ለፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች የስነ ምግባር ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ነው።

ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ ሌሎች የፍትህ አካላት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመዋጋት በሚሰሩት ስራ ከህዝብ አመኔታን ማትረፍና በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

ተቋማቱም የግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር በመዘርጋት ሙስናን የሚፀየፉና መልካም ስነ-ምግባር ያላቸው ባለሙያዎች ለማፍራት መስራት ይገባቸዋል።

ይህ አሰራር ዜጎች በፍትህ አካላቱ ላይ ብቻም ሳይሆን "በመንግስታቸው ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው ለማድረግና ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ ለማጎልበት ይረዳል" ብለዋል።

ስልጠናውን የሚሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው "ሙስናን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የህዝብ አመኔታ ለማግኘትና ችግሩን ለማሸነፍ ከአመራሩ የሚታይና የሚጨበጥ ስራ ሰርቶ ማሳየት ይጠበቃል" ነው ያሉት።

ከአመራሩ ቀልጣፋና ምክንያታዊ ውሳኔዎችን ማሳለፍ፣ የስነ ምግባር አስተምህሮውን አጠናክሮ መቀጠልና ችግሩን በሚፈጥሩ አካላት ላይ ተመጣጣኝ አርምጃም መውሰድ ያስፈልጋልም ብለዋል።

የስልጠናው ተሳታፊ ኮማንደር የኔወርቅ ጋረድ የፌዴራል ፖሊስ በባህሪው ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር እንደሚገናኝ ተናግረው ስልጠናው በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል ብለዋል።

ማህበረሰቡ አንድን ጉዳይ ለማስፈፀም "ህጉን ከመከተል ይልቅ መደለያ ለመጠቀም መሞከርና የፖሊስ አባላትም በእነዚህ አዝማሚያዎች ጫና ላይ መውደቅ" በአብዛኛው የሚያጋጥሙ ችግሮች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ስለዚህም የህብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየርና በፍትህ አካላቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን ሁሉም መስራት አለበት ብለዋል።

ኮማንደር እቋር ሰመረም በተቋማቱ ውስጥ የሚፈጠሩ የስነ ምግባር ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ደንቦች፣ አሰራሮችና ህጎች መኖራቸውን ገልፀው አተገባበራቸውን ማጥበቅ ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

በህዝቡም በኩል የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥር አባል ሲያጋጥመው ለቅሬታ ሰሚና ለቅርብ ሃላፊዎች የሚያጋልጥበት መንገድ ክፍት በመሆኑ በዚሁ መሰረት መብቱን ማስከበር አንዳለበት ተናግረዋል።

ኮማንደር መሰረት ሙሉ በበኩላቸው ችግሩን ታግሎ ለማሸነፍ "የኮሙኒቲ ፖሊስን ማጠናከርና ከህዝቡ ጋር መስራትን ማጠናከር አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን አሰራር ማጠንከሩ የፍትህ አካላቱ ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን ቀረቤታና እምነት ከማጎልበቱ በላይ የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሰራሮችን በቀላሉ መቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።

ስልጠናው ነገም ቀጥሎ እንደሚውል ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን