አርዕስተ ዜና

የመጀመሪያው የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ሊቋቋም ነው

413 times

አዲስ አበባ መጋቢት4/2010 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ሊቋቋም ነው።

ኮንፌዴሬሽኑን የሚያቋቁሙት የአሰሪ ፌዴሬሽኖች ምስረታውን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሰሪዎች፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ውሃና ፍሳሽ አግልግሎት አሰሪዎች፣ የአማራ ክልል አሰሪዎች፣ የአዲስ አበባ አሰሪዎችና የኢትዮጵያ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አሰሪ ፌዴሬሽኖች በጋራ ያቋቁሙታል።

"የአገራችን መልካም እሴቶች በባለ ሀብቱ ወይም በአሰሪው ግንባር ቀደምትነት እንዲጠናከሩና ብዙ ስራ ለብዙ ሰራተኛ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚመሰረተው ኮንፌዴሬሽኑ በዚህ ወር መጨረሻ ይቋቋማል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ጥቃቅን፣ አነሰተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ኃይሌ እንደገለጹት ኮንፌዴሬሽኑን ለማቋቋም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዘርፉ ልምድ ያላቸው አገራትን ተሞክሮ ያካተተ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። 

የኮንፌዴሬሽኑ ምስረታ ዓላማም አሰሪ ፌዴሬሽኖች የአገሪቱን እድገት ሊመጥን የሚችል ሁሉን ያሳተፈና ግልጸኝነት ያለው አደረጃጀት እንዲዘረጉ ማስቻል ነው።

የአሰሪዎች በየዘርፋቸው መደራጀትና መንግስትም ሆነ ሰራተኛው የሁለትዮሽና የሦስትዮሽ ድርድርና ምክክር ከተለያዩ ዘርፎች ጋር ማድረግ አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ ሁሉንም የወከለ አንድ ወጥ አደረጃጀት በማስፈለጉ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የአሰሪውን የመደራደር አቅም ለማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚወክል፣ የእድገቷ ምስክር የሚሆን አምባሳደር ለመፍጠር የኮንፌዴሬሽን መኖር ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት ገልፀዋል።

የአሰሪ ፌዴሬሽኖችን አቅም ማሳደግና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር የሚሰራ ሲሆን በተጨማሪም ማህበራትን ወደ ፌዴሬሽን የማሳደግ ስራም ይሰራል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው ኮንፌዴሬሽኑ አሰሪ ድርጅቶችና ባለሃብቶች የወጣቱን የስራ ፍላጎት ያማከለ ስራ እንዲፈጥሩ ያማክራል፤ አጫጭር ስልጠናዎችንም ይሰጣል ብለዋል።

በአገሪቱ የተሰማሩ የውጭ አገር አሰሪዎች በኮንፌዴሬሽኑ እንደሚታቀፉና እንደየስራ ባህሪያቸው በአገር ውስጥ ፌዴሬሽኖች መመሪያ መሰረት የሚተዳደሩ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው።

ኮንፌዴሬሽኑ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን 87 ድንጋጌዎች እንዲሁም የመስራች ፌዴሬሽኖች ህግና ደንቦች መሰረት ተቋቁሞ በተያዘው ወር ስራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።

Last modified on Wednesday, 14 March 2018 16:36
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን