አርዕስተ ዜና

በወላይታ ሶዶ ከተማ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የፅዳት ዘመቻ ተካሄደ

420 times

ሶዶ መጋቢት 4/2010 በወላይታ ሶዶ ከተማ "ንቅናቄ ለአረንጓዴ፣ጽዱና ሰላማዊ ከተማ"  በሚል መርህ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ ።

የፅዳት ዘመቻው በወላይታ ሶዶ ዞን አስተዳደርና  በወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት ጤራ እንደገለፁት የዘመቻው ዓላማ በህብረተሰቡ ውስጥ የፅዳት ባህልን ለማጎልበት ነው ።

ዘመቻውን በዘላቂነት በማካሄድ  የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓቱን አዘምኖ  የዞኑን ከተሞች ለኑሮ ምቹ ለማድረግ አቅጣጫ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

"በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት ዘመቻው ተካሂዷል" ብለዋል ።

በሁሉም ከተሞች በየ15 ቀኑ ከሚካሄደው የፅዳት ዘመቻ ጎን ለጎን ለህብረተሰቡ በዘርፉ የክህሎት ማሳደጊያ ትምህርት መሰጠት መጀመሩን አመልከተዋል ።

በተለይ የሶዶ ከተማ በየቀኑ በርካታ እንግዶች የሚስተናገድበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና አስተዳዳሪው መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል ።

የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ቡድን ግብ ጠባቂ ወንደወሰን ገረመው በሰጠው አስተያየት  የጽዳት ዘመቻው የከተማዋን ውበት ከማስጠበቅ ባሻገር የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ አስተዋፆኦ እንዳለው ተናግሯል፡፡

"በዘመቻው በመሳተፍ ለሌሎች አርአያ ለመሆን በመቻሌ ደሰተኛ ነኝ " ያለው  ወንደወሰን ከቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል ።

የቡድኑ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አንዱዓለም ሽብሩ ማህበሩ ኳስን ከመደገፍ ባሻገር በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ የመሳተፍ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ከ290 ሺህ በላይ ደጋፊዎች እንዳሉት የገለፁት ፕሬዝዳንቱ በዞኑ በሁሉም ከተሞች በየ 15 ቀኑ በሚካሄደው የፅዳት ዘመቻ በየአካባቢው ያሉ ደጋፊዎች እንዲሳተፉ እንደሚደረግ አመላክተዋል ።

በከተማው የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቄ ቡቴ የአካባቢ ንጽህናን ለመጠበቅ የተጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በሶዶ ከተማ በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ የዞንና የከተማ የሰራ ኃላፊዎች፣ የወላይታ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች እንዲሁም ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን