አርዕስተ ዜና

ትምህርት ቤቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ተባለ

411 times

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2010 በአገሪቷ የሚገኙ 300 ትምህርት ቤቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ መጀመሩን ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ይህን የገለጸው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ለሙከራ የተጀመረውን የዲጅታል ቴክኖሎጂ ወደ ሌሎች ለማስፋት ባዘጋጀው መድረክ ነው።

በመድረኩ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅና ተማሪዎችን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል።

የሚኒስቴሩ የትምህርትና ምርምር ኔትወርክ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም አሰፋ እንደገለጹት ቴክኖሎጂው ዘመናዊ መጻሕፍትንና ሌሎች መረጃዎችን ለተማሪዎች ለማድረስ የሚያግዝ ነው።

በመሆኑም በሁለት ትምህርት ቤቶች የተጀመረውን ቴክኖሎጂ በዚህ ዓመት ወደ 300 ትምህርት ቤቶች ለማሳደግ መንግስት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ማድረግ ዓለም አቀፍ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘትና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሚረዳም አብራርተዋል።

ቴክኖሎጂው ለመማር ማስተማሩ ሒደት የሚጠቅሙ ጽሑፎችን በታብሌቶች በመታገዝ ለተማሪዎች እንዲደርስ የሚያደርግና የመምህራንና የመጽሐፍት እጥረትን የሚያቃልልም ነው ተብሏል ።

"ዓለምን በከፍተኛ ደረጃ ያሳደገና የትምህርት ጥራትን ያረጋገጠውን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ልትተው አትችልም" ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

ሁሉም ነገር ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይህን አለመተግበር ወደ ኋላ እንደሚያስቀርም አክለዋል።

በመሆኑም ከሁለቱ ትምህርት ቤቶች የተገኘውን ልምድ መሰረት በማድረግ በ300 ትምህርት ቤቶች ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አቶ የሱፍ መሐመድ በሙከራ ደረጃ የተተገበረው  የዲጂታል ቴክኖሎጂ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማቀላጠፍ ልምድ የተቀሰመበት በመሆኑ ወደ ሌሎችም ለማስፋት ታቅዷል ብለዋል።

መረጃዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው ለተማሪዎች በሶፍት ኮፒ እንደሚሰራጩና በዲጂታል ላይብረሪ አማካኝነት ስለሚደርሳቸውም ቀደም ሲል በፕላዝማ ሲሰጥ በነበረው ትምህርት የታዩ ውጣ ውረዶችን ቀንሷል ነው ያሉት።

በትምህርት ቤቶች ያለውን የላቦራቶሪ እጥረት መፍታቱን፣ መምህራንም የማስተማሪያ ጽሑፎቻቸውን ለተማሪዎች እንዲያዳርሱ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱን በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ያደረገው ስፖርት ኢጁኬሽን የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አሰፋም  ፕሮጀክቱ ከተተገበረ ሶስት ዓመት ማስቆጠሩንና ውጤታማነቱም በትምህርት ሚኒስቴር መረጋገጡን ገልፀዋል።

በሁለት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሆነው ቴክኖሎጂ ከኢንተርኔት ውጪ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ተማሪዎች በቀላሉ ለማንበብና ከመምህራኖቻቸው እኩል ትምህርታቸውን ለመከታተል እንዳስቻላቸውም አብራርተዋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን