አርዕስተ ዜና

በአገሪቷ 7 ነጥብ 88 ሚሊዬን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

409 times

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2010 በኢትዮጵያ 7 ነጥብ 88 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ለመርዳት የሚያስችል ከጥር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ዓመት የሚቆይ እቅድ ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እንዳብራሩት፣ በአገሪቱ የተከሰቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የተረጅዎችን ቁጥር ከአምስት ነጥብ ሰባት ወደ 7 ነጥብ 88 ከፍ አድርጎታል።

በዚህም አደጋ ያንዣበበባቸውን ዜጎች ለመታደግ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዬን ዶላር እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዛባት በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ ዘግይቶ በመግባቱና ቀድሞ በመውጣቱ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ጨምሯል ብለዋል።

የአሜሪካ መጤ ተምች መከሰት፣ በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች ቶሎ አለማገገም፣ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ጎርፍ የችግሮቹ መንስኤዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ይኸውም የተጎጅዎችን ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረበት አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዬን ወደ ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዬን እንዲያሻቅብ አድርጎታል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች 7 ነጥብ 88 ሚሊዬን ሲሆኑ፤ አንድ ሚሊዬን የሚሆኑት ደግሞ በሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች እና በሌሎች አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት የተፈናቀሉ ናቸው።

በሱማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት 856 ሺ 941 ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውንም ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 67 በመቶ የሚሆኑት ዜጎች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የነበሩና ከክልላቸው ወደ መሃል የገቡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በአገሪቷ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች መካከል አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በገንዘብና በዓይነት የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ በመንግስት፣ በአገር ውስጥ ባለሃብቶች፣ በዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች እርዳታ የሚሸፈን ነው።

ከዚህም በመነሳት መንግስት "በቀጣይ አንድ ዓመት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች አምስት ቢሊዬን ብር መድቧል" ብለዋል።

መንግስት ተጎጅዎችን በሶስት ደረጃ በመለየት፤ "በደረጃ አንድ ለተቀመጡት ለአራት ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ተጎጂዎች ቅድሚያ ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል ኮሚሽነሩ።

ይሁን እንጂ መጠነኛ ችግር አለባቸው ተብለው በደረጃ ሁለትና ሶስት የተለዩ ዜጎች እርዳታ ከዘገዬ ችግሩ ከባድ ስለሚሆን "ሁለቱን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንሰራለን" ብለዋል።

በዚህም መንግስት የገዛው 400 ሺ ሜትሪክ ቶን እህል ከአንድ ወር በኋላ ጂቡቲ ወደብ ላይ እንደሚደርስ ተናግረዋል።

የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ተቋማት አስፈላጊውን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን