አርዕስተ ዜና

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ኅብረተሰቡ በተሳሳተ መረጃ እንዳይደናገጥ ጠንካራ ስራ መስራት ይጠበቅበታል

539 times

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2010 የአገሪቷ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ህብረተሰቡ በተሳሳተና በተፈበረከ መረጃ እንዳይደናገጥ ጠንካራ ስራ መስራት ይጠበቅበታል ተባለ።

 ይህ የተባለው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የበጀት ዓመቱን የስድስት ወር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የስራ አፈጻጸም ለመገምገምና በአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመምከር ባዘጋጀው መድረክ ነው።

 የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደተናገሩት ወቅቱ አገሪቷ በአንድ በኩል ህዳሴዋን ለማረጋገጥ በልማት ስራ ውስጥ፣ በሌላ በኩል ከህብረተሰቡ የተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ ግጭቶች የሚስተዋሉበት ነው።

 በግጭት ምክንያትም ባለፉት 6 ወራት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመፈናቀላቸውና ንብረት በመውደሙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ችግሮች ተከስተዋል።

 በዚህ ውስጥም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የማድረስ ችግሮች እንደነበሩበት ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

 እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የአገሪቷን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የሚጠበቅበት  ኃላፊነት ከፍተኛ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ "ይህንን ሚናውን በሚፈለገው ልክ እየተወጣ አይደለም" ነው ያሉት።

 በመሆኑም ሰላምና ጸጥታ ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የዘርፉ ሚና የጎላ መሆኑን ተረድቶ ህብረተሰቡን በሰላም አጀንዳ በማሳተፍና ትክክለኛ መረጃ በወቅቱ እንዲደርሰው ማድረግ ላይ በፍጥነት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

 ይህ መሆኑ ህብረተሰቡን ከተሳሳተና ከተፈበረከ መረጃ በመጠበቅ እንዳይደናገጥ አቅም እንደሚሰጠው አስረድተዋል።

 በመድረኩ የአገሪቷ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የ6 ወር እንቅስቃሴ ሪፖርት ቀርቦ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በማጣጣም ለሶስት ቀናት የሚቆይ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።

 

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን