በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች እንስሳትን በመግዛት ለምግብነት እንዲጠቀሙ እየደረገ ነው

17 Feb 2017
399 times

ጂግጂጋ  የካቲት  10/2009  በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች እንስሳትን  በመግዛት ለምግብነት እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የእንስሳትና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዓሊ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት ለምግብነት እንዲጠቀሙ እየተደረገ ያለው የክልሉ መንግስት በመደበው 9 ሚሊዮን ብር በጀት  እንሰሳትን ከአርብቶ አደሩ በመግዛት  ነው፡፡

ድርቁ ባለባቸው ሽላቦ ፣ ሺኮሽና  ዋርዴር ወረዳዎች በሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች  በእያንዳንዱ  60 በግና ፍየሎች ከአርብቶ አደሩ በመግዛት ገንዘቡን ለሌሎች ፍላጎታቸው ማሟያ እንዲያውሉት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም  በ47 የውሃ መገኛ  አካባቢዎችና አነስተኛ የህዝብ ቁጥር  ባላባቸው ጣቢያዎች ላይ በየቀኑ 30 ፍየሎችና በጎች በመግዛት ታርደው ስጋውን በቋንጣ መልክ በማዘጋጀት እንዲጠቀሙ እየተሰጣቸው እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

"ድጋፉ በተመሳሳይ ለአንድ ወር የሚቆይ ነው "ያሉት ሃላፊው በቀጣይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲረከቡ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አርብቶ አደር አሊ ፊድ በሽላቦ ወረዳ  የአሊን ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የክልሉ መንግስት በየቀኑ 60 ፊየሎችን  በማረድ ፣ ሩዝና አልሚ ምግብ በማቅረብ  ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለመንግስት ፍየሎቹን በሸጡበት ገንዘብ ስኳር እና ሌሎች የቤት ወጪዎችን በመሸፈን ተጠቃሚ እንደሆኑ አርብቶ አደሩ ገልጸዋል፡፡ 

ከአስር ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ድርቅ  በአካባቢያቸው ማጋጠሙን የተናገሩት አርብቶ አደሩ  አሁን መንግስት የሚያቀርበው የእርዳታ እህል ችግራቸውን ቢያቃልልም በቂ  ባለመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል::

መንግስት በየቀኑ 30 ፊየሎችን በማረድ ሩዝና ስጋ በማቅረቡ ያጋጠማቸው የድርቅ ችግር ለመቋቋም ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በቢርቆድ ወረዳ የሆሳለ ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር  አብዲራን ሂርስ አህመድ ናቸው፡፡

ሆኖም የሚርብላቸው የእንስሳት መኖና መድሃኒት ካለው እንስሳት ቁጥር ጋር የሚመጣጠም  ባለመሆኑ አቅርቦቱ እንዲሻሻልላቸውም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ድርቁ በክልሉ በመማር ማስተማሩ ላይ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመቀነስ ችግሩ በተባባሰባቸው አካባቢዎች ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ 125ሺህ 446 ህፃናት የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምዝገባ መርሃ ግብር  ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ፡፡

በክልሉ ትምህርት ቢሮ የእቅድ ዝግጅት  ሃላፊ  አቶ ፈይሰል አብዲኑር እንደገለጹት ለምዝገባ መርሃ ግብር ማስፈያም ትምህርት ሚኒስቴር 22 ሚሊየን 452 ሺህ ብር  በጀት መድቧል፡፡ ፡

ከተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ለተማሪዎቹ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ እየተመቻቸ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ