አርዕስተ ዜና

ማህበሩ 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ ያካሂዳል

17 Feb 2017
393 times

ባህርዳር  የካቲት 10/2009  የአማራ ሴቶች ማህበር 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።

ጉባኤው ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው " ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራርን በተደራጀ ትግል በመታገል የሴቶች የነቃ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን " በሚል መሪ ቃል ነው።

የማህበሩ ሊቀመንበር ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት፣ በጉባኤው የማህበሩ ያለፉት ሦስት ዓመታት የሥራ እንቅስቃሴ ይገመገማል።

በተጨማሪም በማህበሩ የቀጣይ ሦስት ዓመታት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እንደሚያጸድቅ ሊቀመንበሯ ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላትንና ሥራ አስፈጻሚዎችን ምርጫ ያካሂዳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ማህበሩ በባህር ዳር ከተማ በሊዝ የመነሻ ዋጋ ባገኘው አራት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለሚያስገነባው ሕንጻ የመሰረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ ጠቁመዋል።

በየደረጃው ያለው አመራርና የመንግስት ሠራተኛው በጥልቅ ተሃድሶ ክፍተቶቹን በመለየት ለማስተካከል ቃል የገባበትና ለሴቶች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ በሆነበት ወቅት ጉባኤው መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ማህበሩ ከየካቲት 14 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚያካሂደው 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከ550 በላይ ተሳታፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጥቂት በጎ ፈቃደኛ ሴቶች የተቋቋመው የአማራ ሴቶች ማህበር ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት።

ማህበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም ለማስከበር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ  ነዉ፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ