አርዕስተ ዜና

ጥናትና ምርምሮች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው

17 Feb 2017
370 times

ባህር ዳር የካቲት 10/2009 የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዘባድያ በበኩላቸው እስራኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን የካበተ ልምድና እውቀት ለኢትዮጵያ ለማካፈል በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ 60 የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚቀርቡበት 5ኛው ዓመታዊ የሳይንስ ዘርፍ አውደ ጥናት ዛሬ ተጀምሯል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ባይሌ ዳምጤ በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች ጥልቀት ያላቸውና ለወቅታዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ የሚያበጁ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በተለይ በዘርፉ የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱና ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎችም በዓመታዊ የሳይንስና ምርምር አውደ ጥናቶች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ከዘርፍ ልምድ እንዲቀስሙና ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዘባድያ በበኩላቸው እስራኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን የካበተ ልምድና እውቀት ለኢትዮጵያ ለማካፈል በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

እስራኤል አሁን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ ዜጎቿ ችግሮችን በምርምር በመፍታት አገራቸው ተወዳዳሪና ከበለፀጉ ሃገሮች ተርታ ማሰለፍ እንደቻሉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ወደ ላቀ ከፍታ ለማድረስ የምታደገውን ጥረት ለማገዝ ምሁራንን ወደ እስራኤል በመላክ  በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አገራቸው ያላትን የካበተ ልምድና እውቀት እንዲቀስሙ እየተደረገ  መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ደለለ ወርቁ በበኩላቸው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር አውደ ጥናቱ ተመራማሪዎችን እርስ በእርስ በማገናኘት ልምድና እውቀት የሚለዋወጡበት ነው።

በጥናትና ምርምር ኮንፈረንሱ የሳይንስ ዘርፉን የሚመለከቱ 60 የምርምር ውጤቶች ቀርበው ምክክር ይደረግባቸዋል።

በአውደ ጥናቱ ከሚቀርቡት የምርምር ስራዎች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በወፎች ስደት እያስከተለ ያለውን ተፅኖ፣ በከተሞች የሴቶች የስራ እጥነት ችግር፣ ከአምስተ ዓመት በታች የህፃነት ሞት ቅነሳ የሚሉት ይገኙበታል።

እንዲሁም የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ ማመጣጠን ያለበት ሁኔታ፣ በእንሰት ሰብል ላይ እየተስተዋለ ያለው በሽታና መከላከያው የሚሉትና ሌሎች የምርምር ስራዎች ናቸው።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው አውደ ጥናት ላይ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራንና ተማሪዎች እንዲሁም በዘርፉ ተስፋ የተጣለባቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ