አርዕስተ ዜና

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ከአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ትሆናለች Featured

17 Feb 2017
436 times

አዲስ አበባ የካቲት 10/2009 ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ከአፍሪካ ቀዳሚ አምስት የቱሪስት መዳረሻ አገራት መካከል አንዷ እንደምትሆን አንድ ጥናት አመለከተ።

ጁሚያ ትራቭል የሆቴል ቡኪንግ ኩባንያ ያካሄደውን ጥናት ውጤት ትናንት ይፋ አድርጓል። 

በኢትዮጵያ የቱሪዝም መስክ በተለይም ከሁለት ዓመታት ወዲህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና አገልግሎት ሰጪዎች በፍጥነት እየተስፋፉ መሆኑን ገልጿል።

"ይህም በሚቀጥሉት ዓመታት አገሪቷን ከቀዳሚ የአፍሪካ የቱሪስት መዳረሻዎች ተርታ እንድትሰለፍ ያደርጋታል" ብሏል የኩባንያው ጥናት።

በኢትዮጵያ የኩባንያው ኃላፊ አሌክሳንደር በርትንሻው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ እያገኘች ያለው ገቢ እየጨመረ መሆኑንም አብራርተዋል።

በአገሪቷ የቱሪዝም ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭና የአገር ውስጥ ባለኃብቶች ቁጥርም እያደገ ነው ብለዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለጉብኝት የሚመጡ ቱሪስቶች ስለ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እውነታዎች ያላቸው ግንዛቤም ከፍ ብሏል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረጉ የሚገኙ ዓለም ዓቀፍ ስም ያላቸው ሆቴሎች መስፋፋት ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር ምክንያት መሆኑንም አውስተዋል።

የቱሪዝሙ መስክ በ2007/2008 ዓ.ም ለአገሪቷ ኢኮኖሚው 4 ነጥብ 1 በመቶ ድጋፍ የነበረው ሲሆን ለሥራ ዕድል ፈጠራ 8 ነጥብ 4 በመቶ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በአገሪቷ በመገንባት ላይ ያሉ አምስት ዓለም አቀፍ ሆቴሎችን ጨምሮ 12 ሆቴሎች የቱሪዝም ገበያውን መቀላቀላቸው አገልግሎቱን እንዳዘመነውም ጥናቱ አመልክተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ሆቴል ካላቸው አስር ቀዳሚ አገራት አንዷ ሆናለች ነው ያሉት።  

ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ አብዛኞቹ ቱሪስቶች ለመዝናናትና በክብረ በዓላት ለመታደም መሆኑን የገለጸው ጥናቱ የአፍሪካና አውሮፓ ቱሪስቶች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ጠቁሟል። 

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ታደሰ በበኩላቸው በሆቴል ዘርፍ የሚሰማሩ ባለኃብቶች በመዲናዋ መወሰናቸው በዘርፉ እድገት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ይላሉ።

የሆቴሉ ዘርፍ በፍጥነት እያደገ ቢሆንም በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ባለመኖራቸው የሚፈለገው ለውጥ እንዳልተገኘ ተናግረዋል።

የሆቴልና ሎጂዎች ተደራሽነት በሁሉም አካባቢዎች ቢሆን የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ያስችላል።

"በቀጣይ መንግሥት በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ዋና ዋና መሰረተ ልማቶችን መዘርጋቱን ይቀጥላል" ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ባለሃብቶች በመዳረሻዎች አካባቢ እንዲሰማሩም ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ ብለዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ