በዳንሴ ተፋሰስ 4 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የእርከን ስራ ተከናወነ

11 Jan 2017
1057 times

አዲስ አበባ ጥር 3/2009 በላይኛው ዳንሴ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት በተሰራው የአካባቢ ጥበቃ ስራ 4 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የተራራ ላይ እርከን ስራ ተከናወነ።

የአዲስ አበባ ወንዞች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዛሬ ከመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች ጋር በየካ አንቆርጫ ቀበሌ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የዳንሴ ተፋሰስ ልማት ጎብኝቷል።

በተዳፋት መሬት ላይ የሚከናወነው የዳንሴ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነው ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ ወጣቶች፣ እማወራዎችና  አባዎራዎች በጉልበት ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑ ከጉብኝቱ ለመረዳት ተችሏል።

የአካባቢ ጥበቃ ስራው መከናወን ከጀመረ በአንድ ወር ከ15 ቀን ጊዜ ውስጥ 4 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚሆን የተዳፋት መሬት ላይ እርከን መሰራት ተችሏል።

ከተዳፋት መሬቱ ላይ በዝናብ ወቅት የሚፈጠሩ ጎርፎች ቁልቁል ወርደው ከቀበና ወንዝ እስኪደርሱ በአፈርና በመልከዓ ምድር አቀማመጥ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን ተመልክቷል።

300 ሜትር የድንጋይ መከላከያ 250 ሜትር የድንጋይ እርከኖች እንዲሁም ድንጋይ ለበስ እርከኖችን በመስራት የጎርፍ መጥለቅለቅን ለመካከል ነው እየተሰራ ያለው።

የየካ አንቆርጫ ቀበሌ ከሌሎች በከተማዋ ጠርዝ ከሚገኙ አካባቢዎች የበለጠ ለጎርፍ የተጋለጠ ተዳፋት መሬት በመሆኑ የዳንሴ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ስራውን ፈጥኖ እንደሚያጠናቀቅ ተገልጿል።

በላይኛው ዳንሴ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት የተፋሰስ ልማት ባለሙያ አቶ አንተነህ ወርቁ እንዳሉት በክረምት ወቅት የሚስተዋለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል መሰራት ያለበት ጎርፉ ከሚነሳበት ጋራ ላይ ነዉ።

በጉብኝቱ ወቅት ማየት እንደተቻለው የተፋሰስ ስራው ለአፈር መሸርሸር ተጋላጭ ከሆነው ተዳፋት መሬት በመነሳት የአካባቢው አርሶአደሮች መሬት ድረስ የሚቀጥል ነው።

ከዳንሴ ኮረብታማ መሬት ላይ የሚንደረደረው የክረምት የጎርፍ ውሀ በሚፈስበት መሬት ላይ ገደሎችን እየፈጠረ በመሆኑ ነው የእርከን ስራው ያስፈለገው።

በመሆኑም ስራው የአካባቢውን አርሶአደሮች መሬት ከጉዳት በመጠበቅ የመሬቱን ውሀ የማስረግ መጠን ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል።

በተጀመረው የአካባቢ ጥበቃ ስራ እርከኖችና የድንጋይ ክትሮችን ከመስራት ባለፈ በክረምት ወራት የችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክቱ አስታውቋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ