አርዕስተ ዜና

የሴቶች ስትራቴጂካዊ የልማት ማዕከል ሥራውን በይፋ ጀመረ

11 Jan 2017
412 times

አዲስ አበባ ጥር 3/2009 የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰራ "የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል" በይፋ ሥራውን ጀመረ።

ማዕከሉ የሴቶችን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።

ተመሳሳይ ዓላማ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋርም ማዕከሉ በትብብር እንደሚሰራ ተገልጿል።

ማዕከሉን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳ ሥራውን በይፋ አስጀምረዋል።

በዚሁ ጊዜ ሚኒስትሯ እንዳሉት የሴቶች እኩል ተጠቃሚነትና አጠቃላይ መብቶች በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ላይ በግልጽ የተደነገገ ቢሆንም ተፈፃሚነቱን ለማረጋገጥ የማዕከሉ ዓይነት ተቋማት ወሳኝ ናቸው።

ከዚህ አንፃር ማዕከሉ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና መርሃ-ግብሮች በአፈፃጸም ረገድ የሚስተዋልባቸውን ክፍተቶች በማስረጃ የተደገፈ ጥናትና ምርምር በማከናወን የመፍትሄ ሀሳብ የሚጠቁም እንደሆነ ገልጸዋል።

ማዕከሉ በመንግሥት ደረጃ በሴቶች ጉዳዮች የተያዙትን ዕቅዶች ለማሳካት የሚረዳ በመሆኑ ሚኒስቴሩ በቅርበተ ከመስራት ባሻገር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ወይዘሮ አዜብ መስፍን በበኩላቸው የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰራ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የማዕከሏ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ እንዳሉት በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ሴቶች በርካታ ድሎች መጎናጸፍ ችለዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም በማኅበረሰቡ ውስጥ ሴቶችን አስመልክቶ የሚንጸባረቁ አሉታዊ አመለካከቶች ጨርሰው የተወገዱ ባለመሆናቸውን እኩል ተጠቃሚነታቸውን በሚፈለገው ደረጃ ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራ ይጠበቃል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የማዕከሉ መቋቋም የተሳሳተውን አመለካከት በማረም የሴቶችን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ መመለስ የሚያስችል አስተዋጽኦ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ማዕከሉ ሥራውን በይፋ ሲጀምር በሴቶች ላይ የሚደርሱ ተጽዕኖዎች የሚያሳዩ ዘጋቢ ፊልሞች ለእይታ በቅተዋል።      

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ