አርዕስተ ዜና

የመስህብ ስፍራዎችን ለአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን አመቺ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

11 Jan 2017
656 times

ጎንደር ጥር 3/2009 በሀገሪቱ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች አካል ጉዳተኞችንና አረጋውያን ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባ በዘርፉ የተካሄደ ጥናት አመለከተ።

“የቱሪዝም ተደራሽነት ለሁሉም’’ በሚል መሪ ቃል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለ10ኛ ጊዜ የቱሪዝም ሳምንትን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው፡፡

የበዓሉ አካል በሆነው የቱሪዝም የምርምር ጉባኤ ላይ "የብርሃን ለአለም አለም አቀፍ ድርጅት" አማካሪ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ አብዛኞቹ የሀገሪቱ የመስህብ ቦታዎች ለአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ጎብኚዎች ምቹ አይደሉም፡፡

"በተለይ የመስህብ ስፍራዎቹን ለሚጎበኙ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በምልክት ቋንቋ ገለጻና ማብራሪያ የሚሰጡ አስጎብኚዎች የሏቸውም" ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞችም ሆኑ አረጋውያን የመስህብ ስፋራዎቹን ተዘዋውረው ለመጎብኘት የሚያስችላቸው የተሟላ መስረተ ልማት የሌላቸው በመሆኑ ሲቸገሩ እንደሚስተዋል በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የሚገኙ አብዛኞቹ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ መዝናኛ ስፍራዎችና መጸዳጃ ቤቶችም ቢሆኑ አካል ጉዳተኛ ጎብኚዎችን ታሳቢ በማድረግ የተገነቡ እንዳልሆኑ ጥናቱ ጠቁሟል ።

የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማቱ በብሬል የተዘጋጀ የምግብ ዝርዝር ማውጫዎችና ሌሎችም አገልግሎት የሚሰጡባቸው አሰራሮች እንደሌላቸውም አመልክቷል ።

በአለም ላይ የቱሪዝም ስፍራዎችን ከሚጎበኙ ቱሪስቶች አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ግንባር ቀደም ስፍራ እንደሚይዙ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

አሜሪካ ብቻ ከአካል ጉዳተኞችና ከአረጋውያን ጎብኚዎች በዓመት 13 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የቱሪዝም ገቢ እንደምታገኝ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያም ከቱሪዝም ዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ በማሳደግ በኩል ስፍራዎቹ አካል ጉዳተኞችንና አረጋውያን ጎብኚዎችን ታሳቢ ያደረጉ፣ መሰረተ ልማቶችና በሰለጠነ የሰው ሃይል የተደራጁ ሊሆን እንደሚገባ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

ሌላው ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢ የዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም መምህር  አቶ ዋሴ ጌታሁን "ኢትዮጵያ ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ቢኖራትም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ አናሳ ነው" ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ገቢ ከአፍሪካ በ17ኛ ደረጃ፤ በዓለም ደግሞ በ118ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን የገቢ ድርሻዋም ቢሆን ከ2 በመቶ በታች መሆኑን በጥናታዊ ጽሁፋቸው ጠቁመዋል፡፡

በቱሪዝም ሳምንት በዓሉ ላይ የተገኙት የፌዴራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አሸብር ተክሌ እንደገለፁት የሀገሪቱ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ለአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ጎብኚዎች ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር በኩል ክፍተት አለባቸው፡፡

"በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ ቱሪስቶች የተሟላ መስተንግዶና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ከክልል ቱሪዝም ቢሮዎችና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሰራል" ብለዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በበኩላቸው የቱሪዝም ሳምንት በዓል የሚከበርበት አንዱ አላማ በቱሪዝም ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናት በመለየት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መፍተሄ ለመስጠት መሆኑን ጠቁመዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 10 አመታት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲመራ ከማገዝ አኳያ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮችን በመክፈትና ባለሙያዎችን በማሰልጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከ100 በላይ ለሚሆኑ የክልሉ ቱሪዝም መምሪያዎችና የቢሮው ሰራተኞች የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ነጻ የትምህርት እድል በመስጠት የቱሪዝም ዘርፉን እየደገፈ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ከጥር አንድ ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የቱሪዝም ሳምንት አከባበር የባህል ትእይንት፣ የቁንጅና ውድድር፣ አውደ ርእይ፣ የባህላዊ ስፖርትና የጥያቄና መልስ ውድድሮች ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡

በበዓሉ ላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች፣ የክልልና የፌዴራል የባህልና ቱሪዝም የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ እንግዶች ተሳታፊ መሆናቸውን የዘገበው የኢትዮጰያ ዜና አገልገሎት ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ