አርዕስተ ዜና

በክልሉ ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የክትትል ስራው እንደሚጠናከር ተመለከተ

10 Jan 2017
385 times

ባህርዳር ጥር 2/2009 በየደረጃው በሚካሄዱ በሁሉም የስራ ዘርፎች የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ገለጹ።

በሴቶችን መብትና ጥቅማቸውን የሚጋፉ ችግሮች ለመፍታት በወጡ የህግ ማዕቀፎች ላይ የሚመክር ክልል አቀፍ  የውይይት መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ  አቶ ይርሳው ታምሬ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ባለፉት ስርዓቶች ሴቶች የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መደባዊ ጭቆና ሲፈጸምባቸው ቆይተዋል፡፡

ሴቶችና መላው ህዝቡ ባደረጉት ብርቱ ተጋድሎም ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረውን  ጭቆና ተወግዶ የጾታ እኩልነትና ሌሎች መብቶች በህገ-መንግስቱ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ሴቶች የንብረትና የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ እንዲሁም  የፖለቲካ ተሳትፏቸው እያደገ እንዲመጣ  በመደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ 

አፈ ጉባኤው እንዳመለከቱት ይህም ሆኖ  አሁንም ከሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በማሳደግ   በኩል ውሱንነቶች ይሰተዋላሉ።

ውስንነቶች ለይቶ  በማስተካከል በሁሉም  ዘርፎች የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ክትትልና ቁጥጥሩ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ፈንታየ ጥበቡ በበኩላቸው የውይይት መድረኩ  ዓላማ በመልሶ ማደራጀቱ አዳዲስ የተቀላቀሉ አፈ ጉባኤዎች፣ የሴቶችና ህፃናት አመራሮች የጠራ ግንዛቤ ይዘው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሴቶች ሁለንተናዊ መብት የሚረጋገጠውም ከህዝብ ምክር ቤቶችና መሰል ተቋማት ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ሲቀጥል ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል።

"የስርዓተ ፆታ እኩልነትና የህፃናት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሀገሪቱን እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል" ብለዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ስለስርዓተ ፆታ ጽንሰ ሃሳብ፣ የሴቶች እኩልነት መብት ማክበር የሚያስገኘው ፋይዳና  የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በወጡ የህግ ማዕቀፎች ላይ ተሳታፊዎቹ እንደሚወያዩ ተገልጿል፡፡ ፡

የክልሉ ምክር ቤቱና የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ  በጋራ ባዘጋጁት በዚሁ መድረክ  ላይ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የሚገኙ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የሴቶችና ህፃናት ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ