በክልሉ አንድ ሚሊዮን ሕጻናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ Featured

10 Jan 2017
462 times

ጅግጅጋ ጥር 2/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሕጻናት ላይ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ2017 የመጀመሪያው ዙር የልጅነት ልምሻ በሽታ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዛሬ በክልሉ በይፋ ተጀምሯል፡፡

ለቀናት በሚካሄደው በእዚህ ዘመቻም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ አንድ ሚሊዮን ሕጻናት ክትባቱን ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል።

የክትባት ዘመቻውን ይፋ ለማድረግ ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀ ሥነስርአት ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን ኢስማኤል እንደገለጹት፣  በሕጻናት ላይ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ለእዚህም በክልሉ በሚገኙ 564 ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች በሽታን የሚከላከል የሕጻናት ፀረ አሥር ክትባት በቋሚነት በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በሕጻናት ላይ ሊከሰት የሚችለውን የፖሊዮ በሽታ ለመከላከል ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከፌዴራል ጤና ጠበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተጠናከረ የክትባት ዘመቻ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአሁኑ የክትባት ዘመቻም በክልሉ 93 ወረዳዎችና ስድስት የከተማ አስተዳደሮች ቤት ለቤት በመዘዋወር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቢሮው የተላላፊና ውሃ ወለድ በሽታዎች መቆጣጠሪያ የሥራ ሂደት የጤና ትምህርትና የክትባት ቡድን መሪ አቶ አብዲሸኩር አብዱላሂ በበኩላቸው፣ በዘመቻው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ አንድ ሚሊዮን ሕጻናት ክትባቱን ያገኛሉ፡፡

የክትባት ዘመቻው እስከ ጥር አምስት ቀን 2009 ዓ.ም ቤት ለቤት እንደሚካሄድ ጠቁመው፣ ለዘመቻው ቁጥራቸው ስምንት ሺህ 387 የሚሆን የጤና ባለሙያዎች፣ ተቆጣጠሪዎችና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች መሰማራታቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም 251 ተሽከርካሪዎችና 169 ሞተር ብስክሌቶች ወደተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መሰማራታቸውን ነው የገለጹት።

ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚካሄደው ዘመቻም ሕብረተሰቡ ልጆቹን በወቅቱ በማስከተብ ፖሊዮን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ አብዲሸኩር እንዳሉት ባለፈው ወር በክልሉ በተካሄደው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 956 ሺህ ሕጻናትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ዘመቻውን የዓለም ጤና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መረጃ ድርጅትና የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ