አርዕስተ ዜና

የመከላከያ ሰራዊቱ ኪነ-ጥበብን ለመልካም ገጽታ ግንባታ አለመጠቀሙ ተገለጸ

419 times

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 የመከላከያ ሰራዊት ኪነ-ጥበብን ለመልካም ገጽታ ግንባታ አለመጠቀሙን የዘርፉ ሙያ ማህበራትና ባለሙያዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስቴር 6ኛውን የመከላከያ ሰራዊት ቀን "ህዝባዊ ባህሪያችንን እያጎለበትን ህገ መንግስታዊ ስርዓታችንን በመጠበቅ የአገራችን ህዳሴ ዋስትና ሆነን እንቀጥላለን" በሚል መሪ ሃሳብ በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ይገኛል።

ሚኒስቴሩ ቀኑን አስመልክቶ ከኪነጥበብ ሙያ ማህበራት ተወካዮችና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ስለ መከላከያ ሰራዊት ገጽታ ግንባታ ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።

የሰራዊቱን መልካም ገጽታ በኪነ-ጥበብ ተደራሽ የማድረግ ውስንነት መኖሩን፤ ከሰራዊቱ ውጭ ባሉ የዘርፉ ሙያተኞች የተሰሩትም ቢሆን የማዕረግና የተግባር አለመጣጣም እንዲሁም ሰራዊቱን ትክክለኛ ባልሆነ ስብዕና የመሳል ሁኔታዎች እንደታየባቸው በጥናታዊ ጽሁፎች ተመላክቷል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የኪነጥበብ ሙያ ማህበራት ተወካዮችና የዘርፉ ባለሙያዎች እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ በሌሎች የልማት ተግባራት ያስመዘገበውን ስኬት ያክል ለኪነጥበብ ትኩረት አልሰጠም።

ጋዜጠኛ ሰለሞን አስመላሽ የሰራዊቱ በርካታ አኩሪ ገድሎች በኪነጥበብ እንዳልተደገፉ ይናገራል።

እነዚህ ታሪኮች ከሚጠይቁት ከፍተኛ ፋይናንስ አንጻር በፊልም ሰሪዎች ብቻ ሊከወኑ እንደማይችሉ በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበራትን ወክሎ የተናገረው ሰርፀ ፍሬስብሃት ሰራዊቱ በተለይ በኢንጅነሪንግ ዘርፍ ያስመዘገበውን ስኬት ያህል ለኪነጥበብ ትኩረት አንዳልሰጠ ተናግሯል።

አርቲስት ሰለሞን ሃይሉ በበኩሉ አገሪቱ ካለችበት ፈጣን የቁሳዊ ልማት ጋር ሲነጻጸር የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ብዙም እንዳልተሰራበት ገልጾ፤ የጥበብ ሰዎችና የመከላከያ ሰራዊት ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ተናግሯል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሉተናንት ጄነራል ሐሰን ኢብራሂም የተጠቀሱት ችግሮች እውን መሆናቸውን ተቀብለው፤ይህን መቅረፍ የሚያስችል አደራጃጀት እንደ አዲስ እየተዋቀረ መሆኑን ተናግረዋል።

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጄነራል ሳሞራ የኑስ  በበኩላቸው ከጥበብ ሰዎች ጋር ተባብሮ በመስራት በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን አመለካከትና በተቋሙ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

Last modified on Wednesday, 14 February 2018 00:41
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን