አርዕስተ ዜና

ወጣቱ ትውልድ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለበት ተገለጸ

404 times

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 የሰላም አለመኖር የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት በመረዳት ወጣቱ በሰከነ መንፈስ ለአገሩ ሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባው የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ "በሃይማኖታዊ ስነ-ምግባር የታነጸ ወጣት ለአገር ሰላምና አንድነት ያለው አስተዋጽኦ" በሚል መሪ ሃሳብ በከተማዋ ከሚገኙና ከተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር መክሯል።

በመመክር መድረኩ የተገኙት የሃይማኖት አባቶቹና ተሳታፊ ወጣቶቹ እንደተናገሩት የአገር ሰላም አለመኖር የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት በመረዳት በተለይም ወጣቱ ትውልድ በእውቀትና በክህሎት እየተገነባ በሰከነ መንፈስ ለራሱና ለአገሩ ሰላም ዘብ በመቆም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡

 በዚህም በተለያዩ ጊዜያት ለሚነሱ ጥያቄዎች በትእግስትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመደማመጥ፣ የውይይት ባህልን በማሳደግ እንዲሁም ለዘመናት የተገነባው አብሮ የመኖር እሴቱ እንዳይናድ በማድረግ ረገድ ወጣቱ የሰላም አምባሳደር በመሆን የመሪነት ሚና ሊጫወት ይገባልም ብለዋል።

ወጣቱ በስነ ምግባር ታንጾና አገር ከርእዮተ አለም ልዩነትና ከችግሮች በላይ መሆኑን ተገንዝቦ ቅድሚያ ለሰላም መስጠት አለበት ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ።

ሼክ መሃመድ ሀሰን ሻፊ እንደገለጹት  ወጣቶች የዚች አገር እጣ ፈንታ በትከሻቸው ላይ ያረፈ መሆኑን በመገንዘብ የአገሪቷ ሰላም ተጠብቆ እንዲቆይ ለአፍታም መዘናጋት እንደማይገባቸው አመልከተዋል፡፡

ንቡረ እድ አባ ዮሃንስም በበኩላቸው ሰላም ዋጋዋ የማይተመን መሆኗን ገልጸው ለሰላም ወጣቱ ዘብ መቆም እንደሚገባው አመልክተዋል ።

መነጋገር እንደ አገርም እንደ ዓለምም ከሚያጋጥመን ችግር እንደሚያድነን የሚናገሩት መጋቢ ታምራት አበጋዝም  በትእግስትና በሰከነ መንገድ የመነጋገር የሚገጥሙ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ሀሳብ በመስጠት በመደማመጥ ላይ የተመሰረተ ስራ መሰራት እንደሚገባ አመልክተዋል ።

ወጣቱ ነገሮችን በእርጋታ መመልከት መቻል አለበት ሃይማኖት አለኝ የሚል ወጣት ለአመጽ መነሳሳት እንደሌለበት የሚናገረው ወጣት ባንተአየሁ ታደሰም ነው ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ሰበብ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል።

ይህ የሰላም እጦት ደግሞ ከድህነት ለመውጣት ጥረት እያደረገች ባለች አገር ላይ የሚያሳድረው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ ተጽእኖም ቀላል የሚባል አይደለም።

 

 

Last modified on Wednesday, 14 February 2018 00:30
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን