አርዕስተ ዜና

ኅብረተሰቡ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚስተዋለው የሁከት እንቅስቃሴ እንዲቆጠብ ተጠየቀ

478 times

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የንግድ እንቅስቃሴና የትራንስፖርት አገልግሎት ማቆም ወደ ሁከትና ብጥብጥ እየተቀየረ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የገበያ አድማው የተለየ አጃንዳ ባላቸው አካላት ወደ ሁከትና ብጥብጥ እየተለወጠ በሰው አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኡሚ አባጀማል እንደሚሉት፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከትናንት ጀምሮ የንግድና የትራንስፖርት  እንቅስቃሴ ቆሟል።

"የታሰሩት ይፈቱ፣ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረው ልዩ ጥቅም በቶሎ ወደ ተግባር ይለወጥ" የሚሉት ጥያቄዎች መነሳታቸው ተመልክቷል።

በተለያዩ መንገዶች ተደራጅቶ ጥያቆዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማንሳትና መንግስት ላይ ተጽእኖ መፍጠርን "የክልሉ መንግስት እንደ ችግር አያየውም" ብለዋል ወይዘሮ ኡሚ።

ሆኖም የክልሉ መንግስት እነዚህንና ሌሎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መኖራቸውን በመረዳት ለመፍታትና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ የህግ ታራሚዎችን የመፍታት ስራ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው መልኩ፤ የክልሉ መንግስት መልቀቅ የሚችለውን ከ30 ሺ ሰዎች በላይ መልቀቁን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን እነዚህ ጥያቄዎችና እየተካሄደ ያለው የገበያ አድማ ሌላ ዓላማ ባላቸው አካላት ወደ ሁከትና ብጥብጥ እየተቀየረ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህም በተፈጠረ የእርስ በእርስ ግጭት በዝዋይ፣ በለገጣፎና በጅማ በስምንት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ሲደርስ፤ የግልና የመንግስት ንብረቶች የመሰባበርና የማቃጠል ድርጊት መፈጸሙን አመልክተዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ እየተካሄደ ያለው የገበያ ማቆም አድማም ሆነ እየተከተሉ ያሉት ብጥብጦች የሚያስከትሉትን ጉዳቶች ከግምት በማስገባት ከድርጊቱ እንዲታቀብ አስገንዝበዋል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ያወጣውን መግለጫ በማስታወስም የክልሉ መንግስት የህዝቡን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ለመፍታት ከህዝቡ ጋር እየሰራ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ኡሚ፤ መንግስት በተለያዩ አጀንዳዎች እንዲጠመድ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ድርጊቶቹ በአሁኑ ወቅት እየተፈጠረ ያለውን የመንግስትና ህዝብ ተግባብቶ መስራት ሊያደፈርሱ ስለሚችሉ ሁሉም ከድርጊቱ እንዲታቀብ ጠይቀዋል።

የክልሉ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሁኔታዎች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱና ወጣቶች ስለጉዳዩ ቆም ብለው እንዲያስቡ  እያደረጉ ያሉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉና ጉዳት ያደረሱትን ለህግ በማቅረብና በህግ ማስከበር ስራው ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ቀርቧል።

Last modified on Thursday, 15 February 2018 15:54
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን