አርዕስተ ዜና

በክልሉ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ስራዎችን እንደሚያጠናክር ጋህአዴን አስታወቀ

346 times

ጋምቤላ የካቲት 5/2010 የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የክልሉን መንግስት የሚመራው  የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴምክራሲያዊ ንቅናቄ / ጋህአዴን / አስታወቀ።

በጋምቤላ ከተማ ለአራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው  የጋህአዴን ድርጅታዊ  ኮንፍረንስ  የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ተጠናቋል።

በዚሁ አቋም መግለጫ እንደተመለከተው የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች፣ አድርባይነት ፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የህዝብ ወገንተኝነት መሸርሸር በድርጅቱ የጥልቅ ተሀድሶ ወቅት የተለዩ ችግሮች ነበሩ፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የተለዩት እነዚህን ችግሮች በመፍታት የህዝቡን  ጥያቄዎችን ለመመለስ በተከናወኑት ስራዎች ለውጦች ቢኖሩም በተፈለገው ልክ እንዳልሆነ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት በአቋም መግለጫው አውስተዋል።

በተለይም የመሬት አስተዳደርና አቅርቦት፣ የመንግስት በጀት አስተዳደር፣የትምህርት ጥራት፣ የፍትህ አገልግሎትና የንግድ ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉት ችግሮች ዛሬ ላይም የድርጅቱ ፈተናዎች ሆነው እንዳሉም ተጠቁሟል።

የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩ ችግሮችንና በህዝቡ እየተነሱ ያሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የተጀመረውን ስራ አጠናክረው ለመቀጠል  አመራሮችና አባላቱ  ቃል ገብተዋል።

የወጣቶችና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ስራ  ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ አድረገው  ለመንቀሳቀስ መዘጋጀታቸውንም በአቋም መግለጫቸው አረጋግጠዋል፡፡

በክልል ለተጀመሩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ መሰናክል እየሆኑ ያሉትን የሙስናና ብልሹ አሰራር ፣የአድርባይነት፣ የጠባብነትና ሌሎች ችግሮችን አምርረው ለመታገልም ቃል ገብተዋል።

በክልሉ ያለውን ሰላምና ልማትን በዘላቂነት በማስቀጠል  የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ሌላው የድርጅቱ አመራርና አባላት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ተጠቁሟል።

ከድርጅቱ አመራሮች መካከል ዶክተር ሎው ኡቡፕ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት የጤናና የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑት ስራዎች  አበረታች ቢሆኑም በጥራት ረገድ ከፍተኛ ክፍተቶች እንዳሉ  ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስቀረት በሁሉም መስክ   ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ  ሌላው የድርጅቱ አመራር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ናቸው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ጋትሉዋክ ቱት በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ  "በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን