አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያና አርጀንቲና የሁለትዮሽ ግንኙነት በሁሉም መስኮች ሊጠናከር ይገባል

379 times

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 የኢትዮጵያና አርጀንቲና የሁለትዮሽ ግንኙነት በሁሉም መስኮች ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ ከአርጀንቲና አቻቸው አምባሳደር ፔድሮ ዴልጋዱ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው መክረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጎልበት የሁለትዮሽና የባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም አገራቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአየር ትራንስፖርት መስኮች ለመስራት የጀመሯቸውን ሰምምነቶች ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት መጋቢት 8 ወደ አርጀንቲና ቀጥታ በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የአገራቱን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጉልህ ድርሻ ይጫወታል ብለዋል።

የአርጀንቲና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ፔድሮ ዴልጋዱ በበኩላቸው አገራቸው የቡድን 20 (ጂ-20) ፕሬዚዳንት መሆኗን ጠቅሰው ሁለቱ አገራት በዓለም አቀፍ፣ በመንግስታቱ ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩ ገልጸዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በግብርና እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተባብረው በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውንም አክለዋል።

አርጀንቲና ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መስራት እንደምትሻ መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ጄኔራል ዳይሬክተር አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገልጸዋል።

አርጀንቲና በኢትዮጵያ ያላትን ኤምባሲዋን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2013 በድጋሚ መክፈቷ ይታወቃል።

Last modified on Tuesday, 13 February 2018 21:21
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን