አርዕስተ ዜና

ስምንተኛው የፍትህ ሣምንት በድሬዳዋ መከበር ጀመረ

166 times

ድሬዳዋ ሚያዝያ 8/2010 ጠንካራ የፍትህ ተቋማትን በመገንባት ለሕብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የፍትህ ሳምንት "ጠንካራ የፍትህ ተቋማት ለአስተማማኝ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ በፎቶ አውደ ርዕይ ዛሬ በድሬዳዋ መከበር ጀምሯል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ በዚህ ወቅት እንዳሉት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም የፍትህ አካላት የተካተቱበት የፌደራል አብይ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በእዚህም ጠንካራ የፍትህ ተቋማት፣ ዘመናዊ አሠራሮችንና አደረጃጀቶችን በመዘርጋትና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በማፍራት ለሕብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት በተሰሩ ሥራዎች ጅምር ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።

"በተለይ ሕብረተሰቡ በቅሬታ ለሚያነሳው የፍትህ መዘግየት፣ የፍርድ ጥራት ችግር፣ የቀጠሮ መራዘምና የቀጠሮ ምልልሶችን ለማስተካከል በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ለውጦች ተመዝግበዋል፤ ከቅጣት አወሳሰን ጋር የነበሩ ክፍተቶችም በጅምር ደረጃ መሻሻል ታይቶባቸዋል" ብለዋል፡፡

እንደፕሬዚዳንቱ ገለጻ በየዓመቱ የፍትህ አካላት በውጤት ተኮር የሥራ ምዘና በመታገዝ የተቀናጀ ሥራ መስራት መጀመራቸው በፍትህ ዘርፍ ለውጥ እንዲመዘገብ አግዟል።

እነዚህን ጅምር ለውጦች በአስተማማኝ ደረጃ ለማጠናከርና ለሕብረተሰቡ የተሻለ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት በየዓመቱ የሚከበረው የፍትህ ሣምንት እገዛ እንዳለውም አቶ ዳኜ ተናግረዋል፡፡

የፍትህ ሣምንቱ የሕብረተሰቡን ቅሬታዎች በመሰብሰብ በተናጥልና በጋራ የእርምት እርምጃ ለመውሰድም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

"የፍትህ ሣምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ መከበሩ በፌደራልና በክልሎች ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር የተሻለ የፍትህ አገልግሎት  ለመስጠት ያግዛል" ያሉት ደግሞ በፎቶ አውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፉት የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደምሴ ዱላቻ ናቸወ፡፡

በክልሉ የፍትህ ተቋማትን እስከ ወረዳ በአስተማማኝ መንገድ ተደራሽ በማድረግ ዜጎች ጊዜና ገንዘብ ሳያባክኑ፣ ከሥራቸው ሳይለዩ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይ በፍትህ ተቋማት መካከል ያለውን የቅንጅት ክፍተት በማረም የተሻለ ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

"ባለፈው ሥርዓት የፍትህ ተቋማት ተደራሽ አልነበሩም፤ በአሁኑ ወቅት ዜጎች በራሳቸው ቋንቋ በአቅራቢያቸው እየተዳኙ መሆኑ ለውጥ አለ" ያሉት ደግሞ የቤንሻጉል ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ ናቸው፡፡

ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የፍትህ ሣምንት በዓል በነገው ዕለት በየደረጃው ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና የፍትህ አካላት በተሳተፉበት በፓናል ውይይት ይከበራል።

ዛሬ የተከፈተው የፎቶ አውደርዕይም በድሬዳዋ የሚገኙ የፌደራልና የአስተዳደሩ የፍትህ ተቋማት ለሕብረተሰቡ የፍትህ ሥርአትን ለማስፈን እየሰጡ ያሉትን አገልግሎቶች በሚያንጸባርቅ መልኩ መዘጋጀቱን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

Last modified on Tuesday, 17 April 2018 14:55
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን