አርዕስተ ዜና

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

160 times

ጊምቢ8/2010 በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

አብዱልቃድር አባቢያ እናና አህመድ ኢብራሂም የተባሉት ግለሰቦች አባሪ ተባባሪ በመሆን ከጅማና ቡኖ በዴሌ ዞኖች ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 15 የሚገመቱ ስድስት ታዳጊ ሴት ሕፃናትን በማታለል  ወደ ጊምቢ ከተማ ሲያዘዋውሩ ነው ጥር 4/2010 ዓ.ም. በህረተሰቡ ጥቆማ  የተያዙት፡፡

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኮሙዩኒኬሽን ዲቪዚዮን አስተባባሪ ኢንስፔክተር ስሜነሽ አለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት ግለሰቦቹ ሕፃናቱን በሰው ቤት ሰራተኝነት በማስቀጠር ለጉልበት ብዝበዛ ሊዳርጓቸው አስበው ነበር።

ጉዳያቸውም የፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድንና ዓቃቤ ህግ ሲጣራ ቆይቶ ድርጊታቸው ወንጀል መሆኑን በሰው ምስክርና ማስረጃ በመረጋገጡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ከእስራቱ በተጨማሪ 10ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል።

ግለሰቦቹ ክሳቸውን እንዲከላከሉ  እድል ቢሰጣቸውም ባለመቻላቸው ውሳኔ እንደጸናባቸው ነው ኢንስፔክተሩ ያመለከቱት፡፡

"ሕፃናት ከማያውቁት ሰው ጋር የትም መሄድ የለባቸውም፤ ቤተሰብም ልጆቹ የት እንደሚውሉና ከማን ጋር እንደሚገናኙ መቆጣጠር አለበት"  ብለዋል።

ህብረተሰቡ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ካስተዋለ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ህፃናትን ከጉዳት የመታደግ ኃላፊነት እንዳለበትም ኢንስፔክተሩ አሳስበዋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን