አርዕስተ ዜና

አፍሪካ ሙስናን የሚዋጋ ጠንካራ ስርዓት መፍጠር እንዳለባት ተገለጸ

170 times

አዲስ አበባ 8 /2010 የአፍሪካን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ የህብረቱ አባል አገራት ሙስናን መዋጋት የሚችል ጠንካራ ስርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ።

አፍሪካ በየዓመቱ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ስታጣ ከ148 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደግሞ በሙስና ይመዘበራል።

የአፍሪካ የፋይናንስ እና ገንዘብ ጉዳዮች ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን "አገራዊ ሃብትን በማንቀሳቀስ ሙስናን እና ህገወጥ የፋይናንስ ፍሰትን እንዋጋ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ በህብረቱ አዳራሽ እያካሄደ ነው።

በጉባኤው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ የፋይናንስና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመሩ ሚኒስትሮች ተሳታፊ ናቸው።

የህብረቱን ኮሚሽነር ወክለው ንግግር ያደረጉት የማህበራዊ ጉዳይ ኮሚሽነሯ አሚራ ኤል ፈዲል አንዳሉት፤ ሙስና የአህጉሪቱን ልማት በብርቱ እየተፈታተናት ይገኛል።

"የሙስና ሰብአዊ ጥፋቱ እጅግ የከፋ ነው" ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ችግሩ በተስፋፋባቸው አገራት የእናቶችና ህጻናት ሞት አጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች እንደሚጠቁሙ አብራርተዋል።

ህብረቱ በአፍሪካ በ2063 ሊያሳካው ያቀደው መዋቅራዊ ለውጥ እውን እንዲሆን ሙስናን መዋጋት ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአህጉሪቱ አባል አገራትም ብቁ፣ውጤታማና ፍትሃዊ የግብር ስርኣት በመዘርጋት ሙስናን መዋጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚንስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ በበኩላቸው ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ኢትዮጵያንም እየተፈታተናት  መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ወስዶ ችግሩን ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ጸረ ሙስና ኮሚሽን እና መሰል ተቋማዊ አሰራር በተጨማሪ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም አገራዊ የሙስና ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እየተደረገ መሆኑንም አውስተዋል።

የአፍሪካ የፋይናንስ እና ገንዘብ ጉዳዮች ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ በሚንስትሮች ደረጃ እየተደረገ ባለው ጉባኤ ህገ -ወጥ የገንዘብ ፍሰትን የሚከላከል ተቋማዊ አሰራርን መፍጠር፣ ሙስናን መዋጋትና በአፍሪካ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ዝግጅት ላይ መግባባት ላይ ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

Last modified on Tuesday, 17 April 2018 00:11
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን