አርዕስተ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለገቡት ቃል ስኬት ድጋፍ እናደርጋለን - ነዋሪዎች

242 times

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2010 በተሰማራንበት መስክ የሚጠበቅብንን በመፈጸም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለገቡት ቃል ስኬት ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ባደረጉት ንግግር የበርካቶችን ቀልብ ስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ አበባን ነዋሪ ባገኙበት በዚሁ መድረክ ከህዝቡ አድናቆትና ፍቅር ተችሯቸዋል።

የመጀመሪያ የስራ ጉብኝታቸውን በሶማሌ ክልል፣ ቀጥሎም በኦሮሚያ ክልል አምቦ፤ ከቀናት በፊት ደግሞ በመቀሌ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

"የፍቅርና የአንድነት ኪዳን" በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው የአዲስ አበባው መድረክ በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ እና የፍትህ ሥርዓቱን ለማጎልበት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ ከእያንዳንዱ ዜጋ ምን ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጤታማነት የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለፁት።

ከሐረርጌ አቶ ዩሱፍ አብዱረህማን በሰጡት አስተያየት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻቸውን ሳይሆን  ኢትዮጵያውያን በሙሉ ትንሽ ትልቅ ሳይል መደገፍና አብረን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ አቶ ሚሊዮን ሻምበል በበኩላቸው “መላ ኢትዮጵያዊያን ሲሰማን የነበረው ስጋትና ሰላም ማጣት ተወግዶልን ሰላም ወጥተን መግባት የምንችልበትን ሁኔታ የፈጠሩልን መሪ ናቸው። ሙያችንን እውቀታችንን ተጠቅመን አገራችንን ልዩ ለማድረግ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን።"

"ያደረጓቸው ንግግሮች እጅግ በጣም ማርከውኛል ከልብ ተግባራዊ ሆነው ማየትም እፈልጋለሁ። ለተግባራዊነታቸውም የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ።" ያሉት ደግሞ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኮማንደር ካሳሁን ገብረዮሐንስ ናቸው፡፡

ከጎንደር የመጣው ወጣት ቶፊቅ እስማኤል ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኬት ከጎናቸው እንደሚቆም ነው የገለፀው፤“ለእኛ ለወጣቶች የምንፈልገውን ነገር ነው የተናገሩት ስሜታችንን የሚያነሳሳ ወደ ለውጥ የሚመራን ነገር ነው ፣ ስናግዛቸው ደግሞ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ የእኛ ተግባር ከእሳቸው ጎን መቆም ነው"

የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ሰዒድ ዑመር አሊ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎን በመሰለፍ ለሰላም መስፈን ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቃለ መሃላ በፈፀሙበት ወቅት ከሁሉም ወገን ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነኝ ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

በትናንት ምሽቱ መድረክም የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎችን ለማስቀጠል ህዝብና መንግስት ተቀራርበው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

 

Last modified on Monday, 16 April 2018 23:58
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን