አርዕስተ ዜና

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት የማስፈን ተግባሯን አጠናክራ እንድትቀጥል ተጠየቀ

187 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፈን ኢትዮጵያ የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎቱ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በተመድ የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ጄአን ፕየር ጃክሮኤክሲ ጋር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በምታደርገው ጥረት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ምክትል ዋና ጸሐፊው ኢትዮጵያ ሰላም ለማስከበር እያደረገች ላለው ተሳትፎና እንቅስቃሴ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች የተሰጣቸውን ሰላም የማስከበር ተልዕኮ በመወጣት በኩል ያላቸው ብቃትና ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በኢትዮጵያ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርጅቱ ፍላጎት መሆኑንም ገልጸዋል።

በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል ሰላማዊ ድርድርና እርቅ እንዲመጣና በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክራ እንድትቀጥል ምክትል ዋና ጸሐፊው ጠይቀዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የጎረቤት አገሮችን ሰላምና መረጋጋት ከራሷ ጉዳይ ነጥላ እንደማታየው ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም የማስከበር ተልዕኮዋን ከመወጣት ባሻገር የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በአገሪቱ እርቀ ሰላም እንዲያመጡ የጀመረችውን እንቅስቃሴ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በሶማሊያ ሰላም ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ሁለገብ ተሳትፎ የምታደርግ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ተመድ የሚያደርገውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄ መቅረቡም ተገልጿል።

 

Last modified on Monday, 16 April 2018 22:54
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን