አርዕስተ ዜና

በልማትና ዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ሥራ የድርሻችንን እንወጣለን--- በአፋር ክልል የብዙሃንና ሙያ ማህበራት

255 times

ሰመራ ሚያዝያ 8/2010 በክልሉ በሚከናወኑ የልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሥራ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የብዙሃንና ሙያ ማህበራት ገለጹ።

የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር በክልሉ ለሚገኙ የብዙሃንና ሙያ ማህበራት ለሁለት ቀን በሎግያ ከተማ የሰጠው የአቅም ግንባታ ስለጠና ተጠናቋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የአሌደአር ወረዳ መምህራን ማህበር ተወካይ መምህር አንዳለ በላይ እንዳለው የሙያ ማህበሩ የአባላቱን ጥቅምና መብት ከማስከበር ባለፈ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። 

በቀጣይም ማህበሩ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ከማጠናከር ባለፈ አባላቱን በማነቃነቅ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጎላ ሚና በመጫወት ሥራ ፈጣሪና በሥነምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ከኮሪ ወረዳ ወጣቶች ፌዴሬሽን የመጣው ወጣት ሲሌ ሃቢብ በበኩሉ በህገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን የመደራጀት መብት ተጠቅመው በክልሉ ሰላምና ዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆኑ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል።

"በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ በሚካሄዱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሥራዎች በያገባናል መንፈስ ለመንቀሳቀስ ከመቼውም ጊዜ በላይ የፌደሬሽኑን አባላት አንቀሳቅሰን እንሰራለን" ብሏል።

በተለይ ወጣቶች ከጥገኝነትና ጠባቂነት አመለካከት ተላቀው ወደሥራ በመሰማራት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ፌደሬሽኑ እስከ ቀበሌና ጎጥ ድረስ ያሉ አባላቱን በማስተባበር እንደሚሰራ አመልክተዋል። 

በሰመራ ከተማ የሚገኘው "መኤ-አጎ የአካል ጉዳተኞች ማህብር" ምክትል ሊቀመንበር አቶ መሀመድ ዳርጌ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ለአካል ጉዳተኞች ዝቅተኛ ግምት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይህን አመለካከት ተደራጅቶ ለመከላከልና የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለመረጋገጥ ማህበሩ ባለፉት 10 ዓመታት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ተናገረዋል።

" ይሁንና ማህበሩ ባለበት የአቅም ውስንነትና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ድጋፍ ማነስ የዕድሜውን ያህል እድገት እያሳየ አይደለም " ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም አባላቱ ተደራጅተው ካለባቸው የባህል ጫናና ተረጂነት እንዲላቀቁና እራሳቸውን ችለው በመንቀሳቀስ በክልሉ ልማትና እድገት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማህበሩ በትኩረት እንደሚሰራ አመለክተዋል።

ከሃደለኤላ ወረዳ የመጣችው የወረዳው ሴቶች ፌደሬሽን ሊቀመንበር ወይዘሮ ብርቱካን እንድሪስ በበኩላቸው ሴቶች ካለባቸው የባህል ጫናና ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲላቀቁ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ የልማትና የሰላም እሴት ግንባታ ሴቶች ከወንዶች እኩል የድርሻቸውን ለመጣት ተደራጅተው የጀመሩትን ጥረት በቀጣይም የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል አንደሚሰራ ተናግረዋል።

በፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር የብዙሃንና ሙያ ማህራት ተሳትፎ ዳይሬክተር ጄኔራል ወይዘሮ ሂሩት ደሌቦ በበኩላቸው የብዙሃንና ሙያ ማህበራት ለህብረተሰቡ ያላቸውን ቀረቤታ በመጠቀም በሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚችሉ አመልክተዋል።

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ያለበትን የፖሊሲ ክፍተትና የአፈጻጸም ውስንነቶች ፈጥኖ ለማረም እንዲችል ከብዙሃንና ሙያ ማህብራት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን