አርዕስተ ዜና

መንግስት የዴሞክራሲ ተቋማት ህዝባዊ ተዓማኒነታቸው እንዲጎለብት የማሻሻያ እርምጃዎች ይወስዳል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

160 times

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 8/2010 መንግስት የዴሞክራሲ ተቋማት ከወገንተኝነት ፀድተው ህዝባዊ ተዓማኒነታቸው እንዲጎለብት ጥናት ላይ ተመስርቶ የማሻሻያ እርምጃዎች እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለፁ።

ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ታዓማኒነት ያለው፣ እውነተኛ ፉክክርና የሃሳብ ፍጭት ያለበት እንዲሆን ለማድረግ መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

የዴሞክራሲ እውነተኛ ጥንካሬ ከሚለካባቸው የፍትህ ሥርዓቱ ተቋማዊና ሙያዊ ብቃት ቀዳሚውን ሚና እንደሚይዝ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝቡ የቅሬታ ምንጭ የሆኑት የፍትህ አካላት ነፃነታቸው በሙያዊ የሥነ ምግባር ብቃታቸው እንዲሰሩና በህገ መንግስቱ መሰረት ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።

"ህግና ዴሞክራሲ፤ ፍትህና ብልጽግናን የሚያረጋግጡ መሳሪያዎች እንጂ ሰላምን የሚያጓትቱ መሆን የለባቸውም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በህግና መመሪያ ተከልለው የሚደረጉ አድሎና በደሎች ለማቆም መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የፀጥታ ኃይሎች ተልዕኳቸውን ለማስፈፀምና ሙያዊ ብቃታቸውን ለማሳደግ፣ በህግ የሚሰሩ ህግ ሲተላለፉ ደግሞ በህግ የሚቀጡበትን ሥርዓት ለማጎልበት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

ዴሞክራሲን ለመገንባት የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ ከባድ ስራ መሆኑን አመልክተው፤ ትርጉም ያለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጎለብት ኢህአዴግ ብቻውን የሚፈጥረው ባለመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተጠናክረው መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዘበዋል።

መገናኛ ብዙሃንና በአገሪቷ ዴሞክራሲና ብልጽግና ግንባታ ያላቸው ሚና በቂ ባለመሆኑ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያሳሰቡት።

የመገናኛ ብዙሃኖችና ማህበራዊ ሚዲያ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት እስካሁን ካከናወኑት በይበልጥ አጠናክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት፣ጋዜጠኞችና አመራር አካላት በአገር ግንባታ ሰላምና ልማትን ከማረጋገጥ አኳያ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩም ነው ያስገነዘቡት።

የሃይማኖት መሪዎችም፣ ሰርቆ የመክበር አካሄድን እና ሙስናን በማውገዝ፥ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እሴቶችን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንዲሁም መምህራን ትውልድን በመቅረጽ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን