አርዕስተ ዜና

ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የክልሉ መንግስት ቀዳሚ አጀንዳ ነው - አቶ ለማ መገርሳ

316 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2010 ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የክልሉ መንግስት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ተናገሩ።

የክልሉ አመራር ለተነቃቃው የህዝብ ፍላጎት ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት የክልሉ ምክር ቤት (ጨፌ) 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባዔ የአስፈጻሚውን አካል የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከጨፌው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው።

የክልሉ ዓብይ ተግባር ለወጣቱ የስራ ዕድል መፍጠር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ለማ እንደ ዋነኛ የስራ ፈጠራ ዘርፍ የተለዩና በስፋት የሚኬድባቸው የግብርናና ኢንዱስትሪ መስኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኢንዱስትሪን በማስፋፋት ረገድ መንግስት የተያያዘው የኢንቨስትመንት ስራም ሰፊውን ህዝብ በሚያፈናቅል ሳይሆን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜም የክልሉ መንግስት ለወጣቶች እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ በብድር ያዘጋጀ መሆኑን አውስተዋል።

አቶ ለማ በክልሉም ሆነ በአገሪቷ ሲካሄዱ የነበሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደራቸውን አውስተዋል።

በእንቅስቃሴው የተገኘው ለውጥ ግን አገራችንን ወደ ሌላ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተግተን የምንሰራበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ነው ያሉት።

"አሁን ያለንበት ጊዜ ማንንም የምናማርርበት ሳይሆን ሰርተን የምንለወጥበት ሊሆን ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።

በመሆኑም የክልሉ አመራር ለተነቃቃው ይህዝብ ፍላጎት ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጥበትና ውጤት የሚያስመዘግብበት መሆን እንዳለበትም አክለዋል።

ህዝቡም የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ የማይወጣውን አመራር ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቆ የሚጠይቅበት ጊዜ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው ከፍተኛ የአመራር አባላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

የፍትህ መዘግየት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት አለመረጋገጥ፣ የውሃ አቅርቦት እጥረት፣ የመንገድና የመስኖ ፕሮጀክቶች መጓተትና የኑሮ ውድነት መባባስ ከጥያቄዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

የታየውን ክልላዊና አገራዊ ለውጥ እንዴት ማስቀጠል ይቻላል የሚለውም በአባላቱ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ነበር።

ለተነሱት ጥያቄዎች የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ችግሮቹ በእርግጥም ህዝብ ያስመረሩ መሆናቸውን አምነው ለመፍትሄው ከክልሉ መንግስትና ከጨፌው ጋር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ለመስኖ፣ ለሆስፒታሎች፣ ለመንገዶችና ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች መጓተት የኮንትራክተሮች ብቃት ማነስ፣ የጥናትና ዲዛይን ችግርና አገራዊ የምንዛሬ እጥረት ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።

 

Last modified on Monday, 16 April 2018 00:35
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን