አርዕስተ ዜና

ወጣቶች በተፋሰስ ልማት ያሳዩትን ተሳትፎ በሁሉም ዘርፎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ Featured

12 Jan 2018
267 times

አዲስ አበባ ጥር 4/2010 ወጣቶች በተፋሰስ ልማት እያሳዩት ያለውን ተሳትፎ በሁሉም ዘርፎች አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ባደረገው ርብርብ የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር እንዳስቻለ ያመለከተው ጽህፈት ቤቱ፤  ይህም የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ህይወት በተጨባጭ እንዲሻሻል እገዛ ማድረጉን ጠቁሟል።

የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለመስኖ  ልማት መጎልበት አዎንታዊ ሚና ማበርከቱን በመግለጫው ተመላክቷል።

ከጥር 1 ቀን 2010 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ ከ10 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተገልጿል።

ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ወጣቶች በአገር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ላይ አፍላ ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ እያወጡ መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህን ቁርጠኝነት በሌሎች መስኮችም አጠናክረው  እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።

ወጣቶችን ጨምሮ መላው የገጠሩ ማሀበረሰብ እያካሄደው ላለው የተፋሰስ ልማት ስራ ጽህፈት ቤቱ አድናቆቱን ገልጿል።

የመግለጫው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል:-

 በኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም

መግለጫ- ጥር 4/2010 ዓ.ም.

ወጣቶቻችን በተፋሰስ ልማቱ ላይ እያሳዩት ያለው ተሳትፎ በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!

አገራችን ድርቅን የመቋቋም ጠንካራ አቅም ማጎልበት የቻለችው፣ መንግሥት የነደፈውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ተከትሎ መላው ህዝባችን ባደረገው ያላሰለሰ ርብርብ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነታችንን ለማሳደግ በመቻላችን መሆኑ ይታወቃል። በግብርና ምርታችን ላይ በየዓመቱ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት በምግብ ራሳችንን ከማስቻሉም በላይ የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ህይወት በተጨባጭ መለወጥም ያስቻለ ነው።

የግብርና ምርትና ምርታማነታችንን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ካሉት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መካከል፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ተጠቃሽ ነው። ባለፉት ዓመታት ባካሄድነው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች ክፉኛ ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች ተመልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ ችለናል። ይልቁንም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባላቸው ተክሎች እንዲሸፈኑ በማድረግም የአርሶ አደሩን የምግብ ፍላጎት ከመሟላት ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ አስችሏል። አነስተኛ የአርሶ አደር መስኖዎች እንዲበራከቱ በማድረግም በመስኖ የሚለማውን መሬት በየዓመቱ በእጅጉ እንዲሰፋ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ  የድርቅ ተጋላጭነታችንን መቀነስ ተችሏል። እነዚህና ሌሎች በርካታ ውጤቶች ሊመጡ የቻሉት በገጠር በሚኖረው ሕዝባችን የላቀ ተሳትፎ ነው።

በተመሳሳይ ካለፈው ጥር 1 ቀን 2010 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው  የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ ከ10 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ከፊል አርብቶ አደሮች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።  በአንድ ጊዜ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ በጋራ ወጥቶ የአገራችንን የአየር ንብረት መጠበቅ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነታችንን ማሳደግ እና ግብርናውን ማዘመን በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ መሳተፉ ህዝባችን ከድህነት ለመላቀቅ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያረጋግጥ ነው። በልማቱ ላይ እየተሳተፈ ካለው ህዝባችን ብዙውን ቁጥር የሚይዘው በገጠር የሚገኘው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል መሆኑ ደግሞ ሌላው ሊሰመርበት የሚገባ ሃቅ ነው።

ወጣቶቻችን በዚህ መሰሉ ግዙፍ የልማት ተግባር ላይ በንቃት መሳተፋቸው የአገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገት ከማፋጠን አኳያ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ቀደም ሲል የተመዘገበው ውጤት ያረጋግጥልናል። በመሆኑም ያለፉ ዓመታትን ተሞክሮዎች በመቀመር፣ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት ወደ ስራ የተገባበት የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት በጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚካሄድ ሲሆን በዚህም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል።

እንደሚታወቀው በአገራችን እየተካሄደ ያለው የተፋሰስ ልማት የገጠሩን ህዝብ፣ በተለይም ደግሞ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ዘመናዊና የላቀ ዋጋ ባላቸው የግብርና ሥራዎች ላይ በማሠማራት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ ነው። ካለፍንበት ሂደት እንደምንረዳው በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ወጣት ሞዴል አርሶና አርብቶ አደሮች መፈጠር፣ ለቀጣዩ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ወሳኝ ለሆነው ካፒታል መፈጠር በተፋሰስ ልማት  የተከናወኑ ሥራዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በመሆኑም የገጠሩ ህዝባችን እያካሄደው ላለው የተፋሰስ ልማት መንግሥት አድናቆቱን ይገልጻል። በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል አፍላ ጉልበቱን እያፈሰሰበት ያለው ይህ የልማት ሥራ ነገ ተነገ ወዲያ የእሱን ህይወት በመለወጥ ረገድ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ አገራችንን ከተፈጥሮ አየር መዛባት የሚታደግ እና ዘላቂ ልማቷን የሚያረጋግጥ የአርበኝነት ተግባር በመሆኑ ሊኮራበት ይገባል። በዚህ አጋጣሚ ለተፋሰስ ልማቱ ውጤታማነት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

የአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊሳካ የሚችለው መላው ህዝባችን በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በተፋሰስ ልማቱ ላይ እያሳየው ያለው ቁርጠኝነት በሌሎች መስኮችም ተጠናክሮ ሲቀጥል መሆኑን መረዳት ይገባል። በመሆኑም፣ በከተማም ይሁን በገጠር፣ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ፣ በትምህርትም ላይ ይሁን በሥራ ላይ የምትገኙ ወጣቶቻችን ሁሉ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የተፋሰስ ልማት በመሳሰሉት ታላላቅ ፕሮጀክቶቻችን ላይ ወጣቶቻችን እያሳዩት ያለውን አርዓያነት በመከተል በሁሉም ዘርፍ የተሻለች አገር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አገራዊ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል። 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ