አርዕስተ ዜና

ፓርቲዎቹ በጸረ ሽብር አዋጁ አንቀፆች ላይ በዝርዝር ለመደራደር በቀጠሮ ተለያዩ Featured

11 Jan 2018
275 times

አዲስ አበባ ጥር 3/2010 አገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በጸረ ሽብር አዋጅ ባሉ አንቀፆች ላይ በዝርዝር ለመደራደር በቀጠሮ ተለያዩ።

ፓርቲዎቹ አዋጅ ቁጥር 652/2001ን በሚመለከት ከዚህ በፊት ባደረጉት ድርድር እንዲሻሻሉ፣ እንዲወጡና እንዲጨመሩ የሚፈልጓቸውን አንቀፆች ማቅረባቸው ይታወሳል።

ፓርቲዎቹ አዋጁን በሚመለከት ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ  የተደራደሩ ሲሆን፤ እንዲሻሻሉ፣ እንዲወጡና እንዲጨመሩ ያቀረቧቸው አንቀፆች ላይ  አንድ በአንድ ሳይደራደሩ ጥቅል ሃሳቦችን ሲያንፀባርቁ ውለዋል።

"አዋጁ ከአገሪቷ ህገ - መንግስት ጋር ይጣረሳል” የሚለው ሃሳብ በፓርቲዎቹ ከተነሱ ጥቅል ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በበኩሉ "የፀረ ሽብር አዋጁ በጥቅል ችግር አለበት ከማለት ይልቅ ችግር አለባቸው ተብለው በቀረቡ አንቀፆች ላይ በዝርዝር እንደራደር”  የሚል ሃሳብ በተደጋጋሚ  አንስቷል።

ይሁን እንጂ በዛሬ ውሎ ስለ አዋጁ የተነሱ ጥቅል ጉዳዮች ሰፊ ጊዜ ወስደዋል።

ኢህአዴግ በጊዜ እጥረት ምክንያት በቀረቡ ሃሳቦች ላይ መልስ ባለመስጠቱ፤ በቀጣይ የድርድር  ጊዜ ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ ይዞ እንደሚቀርብ  አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ስለወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን፤ ኢህአዴግ ጥያቄውን መቀበሉን ገልጿል።

ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም በታህሳስ 10 እና 13 ቀን 2010 ዓ.ም ያደረጓቸው ድርድሮችን ቃለ ጉባኤም አፅድቀዋል።

በአዋጁ ላይ ተጨማሪ ድርድር ለማካሄድ ለጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ